ሀዋሳ፡ ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በበዓል ወቅት ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የካፋ ዞን ንግድ፣ ገበያ ልማትና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታውቋል፡፡
ለዚሁ ተግባር ግብረ-ሃይል መቋቋሙን በመግለፅ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን እንዲሆን መምሪያው ጥሪ አስተላልፏል።
የመምሪያው ሃላፊ ወ/ሮ ታሪኳ ታከለ በህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት የተረጋጋ የግብይት ስርዓት እንዳይኖር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበትን ግብረ-ሃይል በማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በበዓል ወቅት እንደ ቅቤ፣ በርበሬና መሰል ምርቶች ላይ ባዕድ ነገሮችን ቀላቅለው መሸጥ ይስተዋል እንደነበር ያነሱት ኃላፊዋ፤ የምርት ጥራትን ከሚመለከተው አካል ጋር በመከታተል መሰል ችግሮች እንዳይኖሩ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የበዓል ወቅት ከፍተኛ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የሚታይበት በመሆኑ የነዳጅ ምርቶችን መደበቅ፣ የተሽከርካሪ እጥረትና የታሪፍ ጭማሪ እንዳይኖር እየተሰራ ነው ብለዋል።
ህገ-ወጥ የነዳጅ ንግድን ለማስቆም በተደረገ ክትትል ከ40 በርሜል በላይ ቤንዚን እና ከ60 በርሜል በላይ ናፍጣ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ገልጸዋል።
በዘርፉ የሚስተዋለዎን ህገ-ወጥነት በቀጣይነት መከላከል እንዲቻልም በዞኑ የሚገኙ 9 የነዳጅ ማደያዎች ከምሽት 12 ሰዓት በኋላ ግብይት እንዳይፈጽሙ በማገድ ችግሮችን መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።
የነዳጅ ግብይት በቴሌብር እንዲሆን አቅጣጫ የተቀመጠ ቢሆንም ከመንግስት መኪናዎች ውጪ ሌሎች ዋጋ ጨምረው በህገ-ወጥ መንገድ እንደሚገበያዩ በመታወቁ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ማስተካከያ ተደርጓል ብለዋል።
እንደ ሀገር በቅርቡ የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ ታይቶ እንደነበር ያነሱት ወ/ሮ ታሪኳ፤ አሁን ላይ በተደረገዉ ጥብቅ ቁጥጥር ወደ ነበረበት መመለስ ችሏል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም መንግስት የፍጆታ ዕቃዎችን በድጎማ ያቀርብ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊዋ፤ ህጋዊ ነጋዴዎችን በማበረታታት የገበያ ሁኔታ ተመጣጣኝ እየሆነ በመምጣቱ በመንግስት ይቀርብ የነበረዉ እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል።
ለመላዉ ኢትዮጵያውያን የእንኳን ለአዲሱ ዓመት ዋዜማ አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ወ/ሮ ታሪኳ፤ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በማቆም የተረጋጋ የግብይት ስርዓት እንዲኖር መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ሸማቹ ማህበረሰብ እንዲያግዝ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ አሰግድ ሣህሌ – ቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ