ሀዋሳ፡ ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በበዓል ገበያ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በመታየቱ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረገ በወላይታ ዞን ሸማቾች ጠይቀዋል፡፡
የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ በበኩሉ የምርት አቅረቦት እጥረት እንዳይከሰት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች መካከል ወ/ሮ ውብቱ ሉቃስ እና ወ/ሮ ምህረት ዮሴፍ በበአል ገበያ የምርት አቅርቦት ቢኖርም የገበያ ሁኔታ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የቀይ ሽንኩርት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ በርበሬ፣ ዘይትና ቅቤ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋቸው መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
ከኢንዱስትሪ ምርቶች የሰኳርና ዘይት ዋጋ መጨመሩን አንስተው የዋጋ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረገ ጠይቀዋል፡፡
በሶዶ ከተማ በመረካቶ ገበያ የዶሮ ነጋዴ የሆኑት አቶ ታረቀኝ ለማ ለዶሮ ገበያ ደረጃ እንዳላቸው በማንሳት ከ5 መቶ ብር እስከ 8 መቶ ብር ዶሮ እየተሸጠ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በወላይታ ዞን አረካ ከተማ የማር ነጋዴ የሆኑት አቶ ኤርምያስ መኮንን በበኩላቸው አንድ ኪሎ ማር 2 መቶ ሃምሳ ብር እየሸጠ እንዳለ አንስተው ከአምና ጋር ሲነጻፀር ብዙ የዋጋ ጭማሬ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
የወላይታ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ ወ/ሮ መብራት ማቴዎስ ለአዲስ ዓመት በዓል የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ እንዲደርሱ አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዘመን መለወጫ በዓል የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን ያነሱት ወ/ሮ መብራት የምግብ ዘይትና ሥኳር አቅርቦት ለበዓል ወቅት እጥረት እንዳይከሰት ከአቅራቢ ማህበራት ጋር በትኩረት እየተሰራ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
የገበያ ሁኔታ ለማረጋጋት የሰንበት ገበያ፣ በህብረት ስራ ማህበራት እና በዩኒየኖች የበዓል መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ለህብረተሰቡ ተደራሽ እየተደረጉ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ በገበያ ላይ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከልም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ድርሻዬ ጋሻው – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የፀጥታ አካላት በየዘመኑ የአገር ክብርና ሉአላዊነትን በማረጋገጥና መስዋዕትነት በመክፈል እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ተናገሩ
ወባን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጸጋዬ ማሞ ተናገሩ
በአዲሱ ዓመት የስንፍናን መንፈስ በማስወገድ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተሰማራበት የስራ መስክ ውጤታማ መሆን አንዳለበት በዳውሮ ዞን የሚገኙ የሀይማኖት መሪዎች አሳሰቡ