ሀዋሳ፡ ነሐሴ 28/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በመድረኩ የፓርላማና የክልል ምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት ዙሪያ የተነሱ ዋና ዋና የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለክልሉ አስፈጻሚ አካላት አቅርበዋል።
ከመራጩ ህዝብ ጋር በሁሉም ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በተካሔዱ ውይይቶች ላይ የተነሱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የመልካም አስተዳደራዊ ጉዳዮች ደረጃ በደረጃ በዝርዝር ለክልሉ አስፈጻሚ አካላት አቅርበዋል።
የክልሉን ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ተግዳሮት የሆኑ የግብርና ግብዓት ስርጭት ውስንነት፣ የአምራች ዘር አቅርቦትና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ችግር በአብነት አቅርበዋል፡፡
የትምህርት ስብራትን መጠገንና የትምህርት ግብአት አቅርቦትን ለማስተካከል አበረታች ተግባራት ቢከናወንም፥ የመምህራን ደመወዝ በጊዜ አለመከፈሉና የመምህራን እጥረት በክልሉ አንዳንድ አከባቢዎች ለትምህርት ስራ ውጤታማነት እንቅፋት መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
ከፀጥታ አንጻር ያሉ ችግሮችን መቅረፍና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ እንደሚገባ የገለጹት የምክር ቤት አባላት፥ ሰላምን ለማጽናት የክልሉ መንግስት በየደረጃው ከሚገኙ አካላት ጋር በቅርበት መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።
በተለያየ ጊዜ ተጀምረው የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶች ጨርሶ ማጠናቀቅና ለህዝብ ጥቅም ማዋል እንደሚገባ ያነሱት የምክር ቤት አባላት፥ የንጹሕ የመጠጥ ውሃ ግንባታ፣ የገጠር ተደራሽ መንገዶችና የድልድይ ግንባታ፣ የህክምና መድኃኒት አቅርቦት ውስንነት፣ የመብራት መቆራረጥ፣ የኔትወርክ ችግር በስፋት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
የኑሮ ውድነትን አባባሽና ሰው ሰራሽ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የገለፁት የህዝብ ተወካዮቹ፥ የስራ አጥ ቁጥር መቀነስና የሸማቾች ጥበቃን ማዕከል ያደረገ የአሠራር ስርዓት ማበጀትና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በፓርላማና በክልል ም/ቤት አባላት ለቀረበው የህዝቦች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ የክላስተር አስተባባሪዎች፥ በየጊዜው እያደገ የመጣውን የዜጎች የመልማት ፍላጎት እውን ለማድረግ በጋራና በቅንጅት መሥራትና የቀረቡ ጥያቄዎችን የእቅድ አካል አድርጎ በግብአትነት የሚወሰድ መሆኑን አስረድተዋል።
ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶችን ከዳር ለማድረስ የገቢ አቅምን ማሳደግና የአፈጻጸም ውስንነቶችን መቅረፍ እንደሚገባ የገለፁት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፥ በዋናነት ግን ቅድሚያ የክልሉን ሰላም ማጽናት ወሳኝ ድርሻ እንዳለው አመላክተዋል።
በስፋት የተነሱት ጥያቄዎች ቀደም ሲል በተለያየ ጊዜ ሲንከባለል የመጣ መሆኑን አስታውሰው፥ ምንም እንኳ ክልሉ አዲስ ቢሆንም ባለው አቅምና እንደ ጥያቄዎቹ ተጨባጭ ሁኔታ የህዝቦችን የልማት ፍላጎት ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻል የብልፅግና ተምሳሌት በማድረግ፥ ከህዝብ እየቀረበ ያለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመመለስ ሁላችንም የየራሳችንን አሻራ ማኖር እንድንችል ተጋግዘን በመስራት የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንችላለን ብለዋል።
በመድረኩ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፣ የክልሉ ምክር ቤት ም/አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ወላይቴ ቢቶ፣ የክልሉ ም/ል ርዕሰ መስተደድርና የኢንተርፕራይዞች ልማትና የስራ እድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገ/መስቀል ጫላ፣ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ እንዲሁም የፓርላማና የክልሉ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
አዲሱ ትውልድ ጀግኖች አባቶቻችን በክብር ያቆዩልንን ሀገር የመጠበቅ ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ መነቴ ሙንዲኖ ገለፁ
የፀጥታ አካላት በየዘመኑ የአገር ክብርና ሉአላዊነትን በማረጋገጥና መስዋዕትነት በመክፈል እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ ተናገሩ
ወባን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጸጋዬ ማሞ ተናገሩ