በደን ቀጠና የሚተገበሩ የልማት ፕሮጀክቶች ከተፈጥሮ ሀብቶች ውድመት ነፃ በሆነና በተቀናጀ ዘላቂ የማህበረሰብ ልማት ስትራቴጂ መተግበር እንደሚገባቸው ተገለጸ

በደን ቀጠና የሚተገበሩ የልማት ፕሮጀክቶች ከተፈጥሮ ሀብቶች ውድመት ነፃ በሆነና በተቀናጀ ዘላቂ የማህበረሰብ ልማት ስትራቴጂ መተግበር እንደሚገባቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ አስገነዘበ።

በክልሉ FOLUR የተሰኘ ፕሮጀክት የማስመጀሪያ መርሀ ግብር በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።

የቡና ምርት ተቀባይ አውሮፓ ሀገራት “ደን ጨፍጭፋችሁ የምታመርቱትን ቡና አንቀበልም” የሚል አስገዳጅ ህግ ማውጣታቸውን ነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሀዝቦች ደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ኢንጂነር አስራት ገብረማሪያም በፕሮጀክቱ ይፋ ማድረጊያ መድረግ ንግግራቸው የገለፁት።

የተፈጥሮ አካባቢን መጠበቅ የሰው ልጅና ሌሎች ፍጥረታት ህልውናን ማቆየት በመሆኑ የትኛውም ልማት የተፈጥሮ ሀብትን የማይጎ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል።

ፕሮጀክቱ እንደሀገር በአራት ክልሎች የሚተገበር ሲሆን በደን ሀብትና ቡና ሽፋን የሚታወቀው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፕሮጀክቱ አካል መሆኑ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

በካፋና ቤንች ሸኮ ዞኖች በስድስት ወረዳዎች በሰላሣ ቀበሌያት የሚተገበረው የዚህ ፕሮጀክት ዋና አላማ ከደን ውድመት ነፃ የሆነ የቡና ልማት ሥራን ከዘላቂ የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ስርዓት ጋር በማስተሳሰር አካባቢን ሳይጎዱ ማህበረሰቡን መጥቀም እንደሆነ ዶክተር አስራት አስገንዝበዋል።

ፕሮጀክቱ ከፈደራል እስከ ቀበሌ በሚዘረጋው የተቀናጀ አመራርና ጥብቅ ክትትል እንደሚተገበር በመጠቆም።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሀዝቦች ደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር በእውቀቱ ሀይሌ አካባቢን ሳይጎዳ በጥራት ማምረትንና ማህበረሰብን መጥቀምን አላማ ያደረገው ፕሮጀክቱ ስላቀፋቸው ተግባራትና የሚጠበቁ አጠቃላይ ግቦች ገለፃ አድርገዋል።

ዘላቂነት ያለውን የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ስርዓትን ከደን ውድመት ነጸ ከሆነው የቡና ልማት ፕሮግራም ጋር ማስተሳሰር እንዲሁም የተራቆቱ ቦታዎችን መልሶ የማልማት ልምዶችን ማበረታታት የፕሮጀክቱ ቁልፍ ተግባር መሆኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር በእውቀቱ በገለፃቸው አመላክተዋል።

የአርሶ አደሩን አቅም ማሳደግም ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት አስተዋፅኦ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

የቡና ልማትና ደን በቀጥታ የተቆራኙ እንደሆኑ ያስረዱት ዶክተር በእውቀቱ፤ ተፈጥሮን የማይጎዳ የተመጋገበ የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ስርዓት ስትራቴጂ ምርትንና ምርታማነትን በማሳደጉ ረገድም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል።

ከፌደራል እስከ ወረዳ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና የመንግስት ተወካዮች በማስተዋወቂያ መድረኩ ላይ የተገኙ ሲሆን ለአካባቢው ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣውን ፕሮጀክት በማስተባበርና በመደገፍ ለውጤታማነቱ እንዲሚረባረቡ ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ወንድሙ ካኪሎ – ከማሻ ጣቢያችን