መምሪያው የ2016 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም እና የ2017 እቅድ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
የንቅናቄ መድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት በ2016 በጀት ዓመት የተከናወኑ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት በቀጣይ ሁሉም የዞኑ ቀበሌያት በመንገድ የማስተሳሰር ስራ ይከናወናል።
ለዚህም ክልሉ የማሽነሪና ሌሎች ድጋፎች ሊያደርግ እንደሚገባ ያመላከቱት አቶ ላጫ፤ ለመንገድ ሰራው በክልሉ በኩል በጀት በወቅቱና በፍትሀዊነት መመደብ እንዳለበት ተናግረዋል።
ከህብረተሰቡ የሚሰበሰበው ገንዘብ በደረሰኝ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው በቀጣይ በጀት አመት በመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን እንግልት የመቀነስ ተግባር በዋናነት የንቅናቄው አካል ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
በመድረኩ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ምስጋና ማቲዎስ በዞኑ የገጠር መንገድ ተደራሽ ለማድረግ የሚሰሩ ተግባራት የሚበረታቱና ለሌሎችም አካባቢዎች በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም በሚሰሩ ስራዎች ክልሉ በቅርበት እንደሚደግፍ አመላክተዋል።
በ2016 በጀት ዓመት በህብረተሰቡ እና በባለሀብቱ የጋራ ቅንጅት 2 መቶ 77 ሚሊየን 3 መቶ ሺህ ብር የተሰበሰበ ሲሆን 2 መቶ 98 ኪሎ ሜትር የአፈር ስራ፣ 2 መቶ 43 ኪሎ ሜትር መንገድ ጠጠር በማልበስ ለትራፊክ ክፍት መደረጉን የዞኑ መንገድ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሙራድ ከድር ገልፀዋል።
የትራንስፖርት ዘርፉን ፍትሀዊ ቀልጣፋና ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ በጀት አመት በዘርፉ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት ይስራል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የዞኑ መንገድና ትራንስፖርት ልማት መምሪያ የ2016 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2017 በጀት አመት እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ህገ ወጦችን ለይቶ ህጋዊ መሰረት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል።
በተለይም ትርፍ መጫን፣ ትርፍ ማስከፈል፣ መንገድ ላይ ማውረድ፣ ደንብና መመሪያን መተላለፍ እና መሰል ችግሮችን ለማረም በሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ህብረተሰቡ የነቃ ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል።
በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚሰሩ የመንገድ ልማት ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚመለከተው ባለድርሻ አካል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
በመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎችም በሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
በመጨረሻም በበጀት አመቱ የላቀ ስራ አፈፃፀም ያስመዘገቡ መዋቅሮችና ለተግባራቱ መሳለጥ የድርሻቸውን ለተወጡ አካላት እውቅናና ሽልማት ተበርክቷል።
ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ