ሀዋሳ፡ ነሐሴ 28/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የፍትህ ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ ሁለንተናዊ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ገልጸዋል፡፡
በዞኑ የማሌና የበናፀማይ ወረዳ ማህበረሰብ በቅርበት የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያግዝ የኮይቤ ምድብ ችሎት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተከናውኗል፡፡
“የፍትህ ተቋማት ተደራሽነት ለብልፅግናችን” በሚል መሪ ቃል ማብሰሪያውን ያደረገው የኮይቤ ምድብ ችሎት በዞኑ በሁለቱም ወረዳዎች በ36 ቀበሌዎች የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍልን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡
የማሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አልጋጋ ባልንሴ በንግግራቸው እንደገለጹት፤ ለዜጎች ፍትህን በቅርበት ለመስጠት የዞኑ መንግስት በማሌ ወረዳ ኮይቤ ምድብ ችሎት መሰየሙ እንዳስደሰታቸው ገልጸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
ለበርካታ ዘመናት የሕዝቦች ጥያቄ ሆኖ የቆየው ፍትህን በቅርበት የማግኘት ጉዳይ ምላሽ ያገኘበትና በወረዳው ፍትህ አገልግሎት የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ መሆኑን አቶ አልጋጋ አክለዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ እንደገለፁት፤ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአዲሱ መዋቅር ዲመካ መሆኑ የፈጠረውን ጫና ለመቀነስ በምክር ቤት ውሳኔ ህብረተሰቡ በቅርበት የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ የኮይቤ ምድብ ችሎት መጀመሩንም አስረድተዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፐቭልክ ሰርብስና የሰው ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳንሳ እንደገለፁት፤ ህዝቡ ለፍትህ ረጅም ርቀት ተጉዘው የሚያወጡትን ወጪ ለመቀነስ የምድብ ችሎት ጉዳያቸውን በአቅራቢያ እንዲታይ ስለሚያግዝ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል መተማመንን ይፈጥራል፡፡
የፍትህ ስርዓቱን ለማሻሻል የህብረተሰቡ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አቶ ንጋቱ ተናግረው ለዚህም ግልፀኝነት ያለው ችሎት መካሄድ እንዳለበትም አንስተዋል፡፡
በምድብ ችሎቱ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር የክልሉ ፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ዳርጌ ዳሼ እና የበናፀማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ጋርሾ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ: ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ጤና ጣቢያው እየሰጠ ባለው አገልግሎት መደሰታቸውን ተገልጋዮች ተናገሩ
የሰላምና የመከባበር ባህልን ለማስቀጠል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ተገለፀ
የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል እንደሚገባ ተገለጸ