የሆሳዕና እናት ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ከአንድ መቶ በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገች
ቤተክርስቲያኗ ለበርካታ አቅመ ደካሞች ጊዜያዊና ቋሚ ድጋፍ እንዲሁም ከ70 በላይ ለሚሆኑ አቅም ላነሳቸው ዜጎች ቋሚ የስራ እድል በመፍጠር መልሶ ማቋቋም መቻሏም ተገልጿል።
የሆሳዕና እናት ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ግርማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የተቸገሩትን መርዳት እና መደገፍ ከእምነቱ አስተምህሮዎች መካከል በመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ድጋፎች በቤተ ክርስቲያኗ ሲደረጉ ቆይቷል።
ከሰባት ዓመታት ወዲህ ተቋቁሞ የተለያዩ በጎ አገልግሎቶችን እያከናወነ በሚገኘው በፍቅርና ርኅራኄ አገልግሎት ህብረት አስተባባሪነት ከምዕመናን የተሰበሰበ የአልባሳት እና የምግብ ቁሳቁስ በዕለቱ ለአቅመ ደካሞች መስጠት መቻሉንም ገልጸዋል።
ከአልባሳት ውጪ አምስት መቶ ሺ ብር የሚገመት የምግብ ቁሳቁስ ለአቅመ ደካሞች የተዘጋጀ ሲሆን በዕለቱም ለአንድ መቶ አስር ዜጎች ዘይትና ዱቄት መሰጠቱን ተናግረዋል። ድጋፉ የሚቀጥል መሆኑን በመጥቀስ።
ወጣት ሙሉ ጸጋ ተስፋዬ የፍቅርና ርህራሄ አገልግሎት ህብረት መሪ ሲሆን ህብረቱ ከተቋቋመበት ከሰባት ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት በጎ ተግባራትን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግሯል።
በፍቅርና ርኅራሄ ሌሎችን መርዳትና ማገልገል የቤተ ክርስቲያን አንዱ ተልዕኮ እንደመሆኑ መጠን ከጎዳና ህፃናት እስከ አረጋዊያን ድረስ ለተቸገሩ ዜጎች ጊዜያዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ከተረጂነት ወጥተው ራሳቸውን በዘላቂነት ማቋቋም የሚችሉበትን የስራ መስኮች የማመቻቸት ስራ ስለመስራቱም የህብረቱ መሪ ወጣት ሙሉ ፀጋ አብራርቷል።
በተጨማሪም የ75 ተማሪዎችን ሙሉ የትምህርት ወጪ በቋሚነት በመሸፈን በግልና በመንግስት ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ መደረጉን የተነገረ ሲሆን የቤት ኪራይ ወጪ የሚሸፈንላቸው አረጋዊያን እና አካል ጉዳተኞች መኖራቸውም ተገልጿል።
ድጋፍ የተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው፤ በዕለቱ ከተደረገላቸው ድጋፍ ባሻገር የልጆቻቸውን የትምህርት ወጪ በመሸፈን እያደረጉ ላለው ሰብዓዊ ተግባር አመስግነዋል።
ድጋፉ የሚደረግላቸው ዜጎች ራሳቸውን ከተረጂነት ለማላቀቅ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት እንዲለወጡ በቤተክርስቲያኗ በኩል ግንዛቤ እንደሚሰጥም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
እመርታ ለዘላቂ ከፍታ!
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የእምርታ ቀንን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት:-
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) መልዕክት፡-