ከግብርና ዕድገት ደረጃ ጋር የተጣጣመና የኢኮኖሚውን ዕድገት የሚያግዝ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የገጠር መሬት መጠቀሚያ ግብር ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚሰራ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 27/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በልዩ ወረዳዉ ከግብርና ዕድገት ደረጃ ጋር የተጣጣመና የኢኮኖሚውን ዕድገት የሚያግዝ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የገጠር መሬት መጠቀሚያ ግብር ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚሰራ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳዳር ገለፀ።

ይህ የተገለፀዉ በገጠር መሬት መጠቀምያ ክፍያና የግብርና ስራ ገቢ ግብር አዋጅ ማስፈፀሚያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በወልቂጤ ከተማ  ዉይይት በተደረገበት ወቅት ነዉ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት የገጠር መሬት መጠቀሚያ ግብር ከዛሬ 16 ዓመት በፊት  የተተመነ መሆኑን በመግለፅ  ከወቅቱ ሁኔታና ከአርሶአደሩ የገቢ ሁኔታ አኳያ የተሻሻለ አዋጅ ነዉ። 

አርሶ አደሩ የተሻሻለው የገጠር መሬት መጠቀሚያ እና የግብርና ስራ የግብር አሰባሰብና አከፋፈል ስርዓትን የተሟላ በማድረግ ለልዩ ወረዳዉ ልማታዊ ተጠቃሚነት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አቶ ሞሳ ገልፀዋል።

በልዩ ወረዳዉ ያለዉን የገቢ አሰባሰብ አሟጦ በመጠቀም በበጀት አመቱ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ በቅንጅት መሰራት አለበት ያሉት ዋና አስተዳዳሪዉ ከግብርና ዕድገት ደረጃ ጋር የተጣጣመና የኢኮኖሚውን ዕድገት የሚያግዝ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የግብርና ስራ ግብር ስርዓት ለመዘርጋት ይሰራል። ለዚህም  ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንዳለባቸዉ አመላክተዋል።

የልዩ ወረዳዉ ገቢዎች ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ በሀሩ ዲጋ በበኩላቸዉ አዋጁ የግብርና ስራዎችን በተገቢው በመለየት በልዩ ወረዳዉ  የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል ።

በገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያ ተመን፣ የግብርና ስራ ግብር ተመን፣ ከፍተኛ ዋጋ ባላቸው የግብርና ምርቶች ገቢ ግብር ክፍያ ተመንና ከእንስሳት እርባታ የሚገኝ ገቢ ግብር ማስፈጸሚያ ተመን ላይ ትኩረት ያደረገ አዋጁ መሆኑን የገለፁት ሀላፊዉ ይህም እስከዛሬ በልዩ ወረዳዉ ገቢ መሰብሰብ ባልተቻለባቸዉ የግብርና ስራዎችን በተገቢው በመለየት የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ የሚያግዝ ነዉ ብለዋል።

ሀላፊዉ አክለዉም የገቢ መረጃን በተገቢዉ በማደራጀት ከገጠር መሬት መጠቀሚያ የሚገኘውን ሀብት ለመሰብሰብ  ቅንጅታዊ ስራዎች ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

በዉይይት መድረኩ አዋጁን በተመለከተ ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት ቀርቦ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

በልዩ ወረዳዉ የገጠር መሬት መጠቀምያ ክፍያና የግብርና ስራ ገቢ ግብር አዋጅ ማስፈፀሚያ  የወጣውን ደንብ ተፈጻሚ ለማድረግ ከተሳታፊዎች የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ወልቂጤ ጣቢያችን