የህብረት ሥራ ዩኒየኖችን በመጠቀም ለህብረተሰቡ አስፈላጊ ምርቶች በቂ አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ የተረጋጋ ገበያ እንዲፈጠር እየሰራ መሆኑን የኮንታ ዞን ንግድ፣ ገበያ ልማትና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታውቋ፡፡
አቶ በላይ ወርቁና ወ/ሮ ሰናይት ብርሃኑ በዞኑ የአመያ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ ከአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማግስት ያልተጠበቀ የዋጋ ጭማሪ በሁሉም ምርቶች የተከሰተ ቢሆንም መንግስት በወሰደው አስተዳደራዊ እርምጃ የዋጋ መሻሻሎች መታየታቸውን ተናግረዋል።
የአመያ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ተስፋሁን አየለና በዞኑ የኮንታ ኮይሻ ወረዳ ነዋሪ ወጣት እንባቆም ከንፈሸ አንዳንድ ነጋዴዎች የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ባልተገባ መንገድ በመረዳት ምርቶችን መደበቅና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ቢሆንም መንግስት በፈጠረላቸው የግንዛቤ ሥራ እንዲሁም የተለያዩ ማህበራትን በመጠቀም የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በማቅረብ ገበያውን ማረጋጋት ተችሏል ብለዋል።
ተቋርጦ የነበረው በመንግስት ድጎማ የሚቀርቡ የፍጆታ ምርቶችን በማቅረብ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጉ መንግስት የዋጋ ጭማሪ ለማሻሻል የወሰደውን ጥረት ያመላክታል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የበዓል ገበያ በአሁኑ ወቅት የግብይት ሥርዓቱ የተሻለ መሆኑን እና መንግስት ህገ-ወጥ ደላሎችን ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ በቅርበት ገበያውን የመከታተልና አቅርቦት ላይ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ በመሆኑ ለበዓል ገበያው አጋዥ እንደሆነ ተመላክቷል።
በዚህም ገበያውን በማረጋጋት ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የግብርና ምርቶችንና በመንግስት ድጎማ የሚቀርቡ የፍጆታ ምርቶችን እንዲያገኝ ማስቻሉን የዞኑ ንግድ፣ ገበያ ልማትና ኢንቨሰትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመስገን ደጀኔ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የተለያዩ የአካባቢ ምርቶች ወደ ገበያ ሲቀርቡ በህገ-ወጥ ደላሎች እየተወሰዱና ከፍተኛ በሆነ የዋጋ ጭማሪ ገበያው እንዳይረጋጋ የማድረግ ሁኔታ ቢኖርም አሁን ላይ የበዓል ገበያ ወቅት በመሆኑ ህዝቡ ለህገ-ወጥ ደላሎች እንዳይዳረግ አምራቹን ቀጥታ ከሸማቹ ጋር የማገናኘት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ተመስገን ገልጸዋል።
አንዳንድ ባልተገባ መንገድ የምርት እጥረት እንዳለ በማስመሰልና ነገ እጥረት ይኖራል በሚል ግምት ህዝቡ ላልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚዳርግ አካል ከተገኘ ጥቆማ እንዲሰጥ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ አብዮት እሸቱ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ