ከ10 ሺህ በላይ የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ተሰማርተዋል- አቶ ዳጋቶ ኩምቤ

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀምና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሚዛን ከተማየውይይት መድረክ አካህዷል፡፡

መድረኩን የመሩት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እንደገለፁት ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ጉልህ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

በዚህም ከውጭ ሀገር የሚመጡ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ የመጣ ሲሆን በሀገር ውስጥ ያሉት ኢንቨስተሮች ላይም መነቃቃት ተፈጥሯል ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም የውጪ ሀገራት አልሚ ባለሀብቶችን ለመሣብ በተደረገው ጥረት ከ10ሺህ በላይ ኢንቨስተሮች በ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር  ካፒታል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቶች ላይ ተሳትፈው ኢንቨስት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

በዘርፉ እየተከናወነ የሚገኘው አበረታች ሥራ በአፍሪካ ከግብፅና ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ ሦሥተኛ ደረጃ ላይ በመሆን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገር ተደርጋ እንድትቆጠር አድርጓታል ብለዋል አቶ ዳጋቶ።

ምክትል ኮሚሽነሩ አክለው በ2016 በጀት ዓመት 12 ሺህ አዳዲስ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራት ባለሀብቶች ፍቃድ ማውጣታቸውን ጠቁመዋል።

በአዲሱ በጀት ዓመትም የውጭ ባለሀብቶችን በመሣብና የሀገር ውስጥ ባለሁበቶችን በማበረታታት የተጀመረውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ በመተግበር ሀገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ በውይይቱ  ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ መድረሱንም አስረድተዋል።

ባለፉት ዓመታት በመስኩ ያጋጠሙትን እንደ መሰረት ልማትና መሬትን ከካሳ ነፃ አድርጎ ለኢንቨስተሮች ማሣለፍ ላይ የታዩት ተግዳሮቶችን በሚቀጥሉት ጊዜያት ለመፍታት አቅጣጫ መቀመጡንም ገልፀዋል ፡፡

በዘርፉ የታዩ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም አብራርተዋል።

ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ- ከሚዛን