ሀዋሳ፡ ነሐሴ 26/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የቱርካና ሀይቅ ከተፈጥሮ ፍሰቱ ውጭ መሆኑን ተከትሎ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል በተሠራው ስራ ዙሪያ ከዳሰነች ነዋሪዎች ጋር መክረዋል።
የአደጋውን መጠን ለመቀነስና ለመከላከል የተሠራውን ስራ ሪፖርት ያቀረቡት የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊና የአደጋ መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ባንኬ ሱሜ፤ የሃይቁን ሙላት ተከትሎ በዜጎች ላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት እንዳይደርስ ለማስቻል የተከናወኑ ተግባራትን ገልጸዋል።
አካባቢው 66 በመቶ በውሃ ተሸፍኗል ያሉት ኃላፊው፥ በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት ከስጋት አካባቢ ወደጊዜያዊ ማቆያ የማስፈርና ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ እና ለእርሻ ተስማሚ የሆኑ ለም መሬቶች በሙሉ በውሃ መያዛቸውን ገልጸዋል።
የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በተለይም የአካባቢ አስተዳደር እንደ ቀበሌና ጤና ኬላ ያሉ ተቋማት በውሃ መዋጣቸውን ተከትሎ ተጨማሪ አደጋ አባባሽ ችግሮች እንዳይከሰቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን አመላክተው፥ የሃይቁን ከተፈጥሮአዊ ፍሰቱ ውጭ ሆኖ የመጣውን ውሃ ማሽኖችን በመጠቀም የውሃ ማፋሰሻ የማበጀት ስራዎችን ማከናወናቸውን አስረድተዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፥ በአጭር ጊዜ ሊሰሩ የሚገቡ ጉዳዮችን ጠቁመው፥ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከስጋት አካባቢ ወደጊዜያዊ ማቆያ ማስፈርና ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ማድረግ እንደሚገባ አመላክተው የክልሉ መንግስት የድርሻውን ኃላፊነት ይወጣል ብለዋል።
ይህንን ጊዜያዊና ወቅታዊ ፈተና በትዕግሥት መሻገር ይገባናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በዋናነት ትኩረታችን አደጋውን መቀነስ ላይ መሆኑን አመላክተው፥ ሌሎች ጉዳዮች በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ምላሽ እንዲያገኙ በየደረጃው ከፌደራል፣ ከክልል እና ከዞን ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
ማሽኖችን በመጠቀም ጊዚያዊ የውሃ ማፍሰሻ እና የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በየዓመቱ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ ለመቀነስ ውሃው ሰው ላይ ጉዳት ሳያደርስ መጠቀም የምንችልበትን መንገድ በጥናት በመለየት መስራት እንደሚገባ አሳስበው፥ ለቱርካና የቀረቡ ቀበሌ ነዋሪዎችን ከአካባቢው በማራቅ አስፈላጊውን መሰረተ ልማት ለሟሟለት ከረዥም ጊዜ አኳያ አቅደን የምንሰራው ይሆናል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ