የከተማዋን መሠረተ ልማት ለማስፋፋት በሚደረገው ሂደት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የቀለጣ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

የከተማዋን መሠረተ ልማት ለማስፋፋት በሚደረገው ሂደት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የቀለጣ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

በነዋሪውና ባለድርሻ አካላት ቅንጅት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የገንዘብ ወጪ በማዳን የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታና የውኃ መሠረተ ልማት ስራዎች መከናወናቸውን የቀለጣ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ገልጿል።

በ1988 ዓ/ም የተቆረቆረችው የቀለጣ ከተማ አሁን ላይ በነዋሪውና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ለከተማው እድገት ካላቸው ፍላጎት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡባት ይገኛል።

ከተማው ፈጣን የከተማ እድገት በማሳየት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፈርጅ አምስት ወደ ፈርጅ አራት ደረጃ ማደጉን ተከትሎ  ሁሉ አቀፍ የልማት ተሳትፎ በማድረግ የሚጠበቅባቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ካነጋገርናቸው የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ኤርምያስ ለዕላጎ እና አበበ አለዬ ማዘጋጃ ቤቱ የከተማውን ነዋሪ በማሳተፍ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የከተማውን የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታን ጨምሮ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የከተማው ነዋሪ በሳምንት ሁለት ቀን ነፃ የጉልበት ተሳትፎ በማበርከት ዓይነተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሆነም ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።

የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የድርሻውን እንደሚወጡ የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ: በመብራት መሠረተ ልማት ዝርጋታ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ባለድርሻ አካላት መፍትሄ እንዲያበጁ ሲሉም ጠቁመዋል።

የቀለጣ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሄኖክ መንግስቱ እንደገለጹት የነዋሪውንና የባለድርሻ አካላትን የልማት ተሳታፊነት በማጎልበት በአሁኑ ወቅት አዳዲስ የውስጥ ለውስጥ መንገድና የውኃ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።

ከተማው ለነዋሪው ምቹ፣ ሳቢና ጽዱ እንዲሆን ከማድረግ አንፃር የከተማ መሪ ፕላን የተከተሉ የከተማ ልማት ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ሄኖክ ነዋሪው በየሳምንቱ ሁለት ቀን ነፃ የጉልበት ተሳትፎ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

በከተማው የሚገኙ የወጣት ማህበራትን ጨምሮ አመራሩና ባለሙያው ባደረገው የተቀናጀ ርብርብ በህብረተሰብ ተሳትፎ የ48 ኪሎ ሜትር የውኃ መስመር ዝርጋታ ቁፋሮና የአዳዲስ መንገድ ከፈታ ስራዎች በማከናወን ይወጣ የነበረውን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉንም ምክትል ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል።

ከተማውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተቀናጀ የከተማ ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና 4 ሺ ካሬ መሬት ለኢንቨስትመንት መዘጋጀቱም ተጠቁሟል።

ዘጋቢ: ጡሚሶ ዳንኤል ከሆሳዕና  ጣቢያችን