የኮሬ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ዩኒት የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አጥ ልየታ የንቅናቄ መድረክ አካሄደ

የንቅናቄውን መድረክ በንግግር የከፈቱት የኮሬ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ፣ የግብርና መምሪያ ኃላፊና የመሠረተ ልማትና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አስታረቀኝ አንደባ፤ ወጣቱ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆንና በህብረተሰቡ ዘንድ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖር በገጠር አዋጅ በሚፈቅደው መልክ ወጣቱ እንዲያለማ ማስቻል እንዲሁም በከተማ ወደ ዘመናዊነት በሚያሻግር መልኩ ለወጣቱ ሥራ መፍጠር ይጠበቅብናል ብለዋል።

የ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀም ያቀረቡት የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ዩኒት ባለሙያ አቶ ዜና ይገረሙ 3 ሺህ 3 መቶ 32 ወጣቶችን በቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ2 ሺህ 2 መቶ 18 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩንና አፈጻጸሙ 66 ነጥብ 5 መሆኑን ገልጸዋል።

በተያዘው 2017 በጀት ዓመት ምርትና ምርታማነትን በሚጨምሩ ተግባራት ላይ በጊዜያዊና ቋሚ ሥራ ዘርፍ ለወጣቱ ሥራ ለመፍጠር የልየታ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በኮሬ ዞን የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ጢሞቴዎስ በቀለ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ሰው ተኮር በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊመራ የሚገባ መሆኑን በመግለጽ የ2016 በጀት ዓመት ተግባር ከሥራ አጥ ልየታና ብድር አመላለስ በስተቀር ሌሎች ተግባራት ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስረድተዋል።

በኮሬ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ዩኒት መሪ አቶ በላይ በየነ በበኩላቸው ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠር በከፍተኛ የልማት ዕድገትና የኢኮኖሚ ጀርባ አጥንት በመሆኑ በርካታ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ተጥሎ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከተሳታፊዎች አቶ አጥናፉ ሰለሞንና አቶ አስፋው ግዛው ወጣቱን የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለማድረግ ቁጠባ ከራሳችን በመጀመር በቋሚ 80 በመቶ በጊዜያዊ 20 በመቶ ማሳካት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ዘጋቢ: ምርጫ መላኩ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን