የጋሞ ዞን አስተዳደር ቅድሚያ ለሚሹ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ትኩረት እንደሚሰጥ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዞኑ የሚታየውን የመንገድ፣ የውሀና መሰል የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲያስችል ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡትን በማስቀደም እንደሚሰራ የጋሞ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

የጋሞ ዞን ህዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 10ኛ አመት የስራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ጉበኤ እያካሄደ ይገኛል፡፡ ጉባኤው የ2016 እቅድ አፈጻጸም ላይ ተወያይቷል፡፡

በግል ጤና ተቋማት ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ በ20 የግል የጤና ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱም ተመላክቷል።

ከመሬት ሀብት ጋር ተያይዞ የደላላ መበራከት ብልሹ አሰራር እንዲስፋፋ ማድረጉን፤ በካዳስተር ረገድ የጎላ ችግር እየታየ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ የክትትልና የቁጥጥር ስራው እየተጠናከረ መሆኑንና ህብረተሰቡ ሊያግዝ እንደሚገባ ተገልጿል።

በአርባምንጭ ከተማ 15 ሺ ህጋዊ የመሬት ይዞታዎች ያሉ ቢሆንም 29 ሺ ህገ ወጥ ይዞታዎች መኖራቸው መረጋገጡንና ይህን ለማረም ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ መሆኑ ተመላክቷል።

በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን የንጹህ መጠጥ ውሀ ችግር ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ስራ እንደሚያስፈልግ ተነስቷል።

የጋሞ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ዞኑን ከሌሎች ዞኖችና ወረዳን ከወረዳና ከቀበሌ ጋር የሚያገናኙ የመንገድ መሠረተ ልማቶች በአግባቡ እንዲከናወኑ በቀጣይ ሰፊ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የጨንቻ ሆስፒታል የመመርመሪያ መሳሪያ የማሟላት ስራ በቀጣይ እንደሚሰራና የደራማሎ ሆስፒታል ግንባታን ከማገዝ አኳያ ጥረት እንደሚደረግ አንስተዋል።

የዞኑን የገቢ አቅም በይበልጥ ለማሳደግ ያልተነኩ የገቢ አማራጮችን በመለየት መስራት ያስፈልጋል ያሉት አቶ አባይነህ በእንሰት ላይ በደንብ መስራትና ቴክኖሎጂውን በይበልጥ ማሻሻልና ማስፋት ይገባል ብለዋል።

የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎችን በማጠናከር ተራራማ ቦታዎች ላይ የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

በጉባኤው የ2017 በጀት አመት እቅድ ቀርቦ ተጨማሪ አስተያየት የተሰጠበት ሲሆን ለበጀት አመቱ እቅድ ማስፈጸምያ እንዲሆን 8 ቢሊዮን 320 ሚሊየን 383 ሺህ 020 ብር በጀት በማፅደቅ ጉባኤው ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን