ተቋማዊ አሰራሮችን በማዘመንና ግልፀኝነትን በመፍጠር በቢሮው የተጀመሩ ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ መረባረብ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ተቋማዊ አሰራሮችን በማዘመንና ግልፀኝነትን በመፍጠር በቢሮው የተጀመሩ ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ መረባረብ እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑሪዬ ገለፁ፡፡

ቢሮው በ2017 በጀት አመት በተከለሰ የበጀት ዕቅድ እና በዋና ዋና የተቋሙ ግቦች ዙሪያ ከተቋሙ ስራ አመራር አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡

ዶ/ር መሀመድ ኑሪዬ በዚህ ወቅት እንደገለፁት ዕቅድ ላይ የተሻለ ተግባቦት በመፍጠር ወደ ተግባር መግባት ለታቀዱ ዕቅዶች ውጤታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው፡፡

በመሆኑም ግልፀኝነት መፍጠር የሚያስችሉ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀትና ተቋማዊ አሰራሮችን በማዘመን የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ መረባረብ እንደሚገባ ዶ/ር መሀመድ ተናግረዋል፡፡

የመረጃ አያያዝና ልውውጥን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመው በተለይም ከልማዳዊ አሰራር በመላቀቅ መረጃዎችን ቀድሞ ማደራጀትና በቴክኖሎጂ ማዘመን እንደሚገባ በመግለፅ በ2016 በጀት አመት የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠልና ውስንነቶችን በመቅረፍ በ2017 በጀት አመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ በሚከበሩ የመስቀልና የአዲስ አመት በዓላት ተሳፋሪዎች ሳይቸገሩ የትራንስፖርት አገለግሎት እንዲያገኙና የትራንስፖርት ፍሰቱ ከትራፊክ አደጋ የፀዳ እንዲሆን ከወዲሁ ልዩ ዕቅድ ማዘጋጀት እንደሚገባም ዶክተር መሃመድ አስታውቀዋል፡፡

የቢሮው ምክትልና የመሰረተ ልማት ክላስተር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አማን ኑረዲን በበኩላቸው በተለይም የተመደበውን በጀት በአግባቡ ለታለመለት አላማ እንዲውል እንደ ቢሮ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ተግባራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡

በበጀት አመቱ የተያዙ ዋና ዋና ግቦችን ለማሳካት ከተጠሪ ተቋማት እንዲሁም ከዞንና ልዩ ወረዳዎች ጋር የውል ስምምነት በመፈራረም ወደ ተግባር ተገብቷል ያሉት አቶ አማን፤ በውይይቱ የተነሱ ሀሳቦች እንደግብዓት እንደሚወሰዱ ተናግረዋል፡፡

ከተሽከርካሪ ታርጋና መንጃ ፍቃድ ህትመት፣ በዩራፕ መንገዶች አፈፃፀም፣ በተቋሙ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን ከማስቀጠል፣ የሚወጡ መመሪያዎችና ደንቦችን በአግባቡ ስራ ላይ ከማዋል እንዲሁም ከሰሌዳ ሊብሬና ቦሎ ህትመት ጋር ተያይዞ ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የተቋሙ ስራ አመራር አባላት በሰጡት አስተያየት ከተጠሪ ተቋማትና መዋቅሮች እንዲሁም ከተቋሙ የስራ ክፍሎች ጋር ጠንካራ የስራ ግንኙነትና የመረጃ ልውውጥ በመፍጠር በ2017 በጀት አመት በተቋሙ የተያዙ ዋና ዋና ግቦችን ለማሳካትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን