ሀዋሳ፡ ነሐሴ 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጎፋ ዞን ህዝብ ምክር ቤት አራተኛ ዙር መርሀ ግብር 11ኛ ዓመት የስራ ዘመን ስምንተኛ መደበኛ ጉባኤ በሳውላ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
ምክር ቤቱ በዞኑ በደረሰው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች የሕሊና ፀሎት በማድረግ ነው ጉባኤውን ማካሄድ የጀመረው።
የጎፋ ዞን ህዝብ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ አበበች መርጊያ የዞኑን ምክር ቤት አራተኛ ዙር መርሀ ግብር 11ኛ ዓመት የስራ ዘመን ስምንተኛ መደበኛ ጉባኤ ሲከፍቱ እንዳሉት በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶችና አስፈጻሚ አካላት ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችና ለህግ የበላይነትን መረጋገጥ ልዩ ትኩረት መስጠት አለባቸው።
ምክር ቤቶች የሕዝቡ ዘላቂ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ እንዲሁም መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።
በየተቋሙ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን በመታገል በዞኑ ዘላቂ ልማትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት የህልውና ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ህግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ህግ ተርጓሚው የየራሱን ድርሻ በተገቢው መወጣት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በጉባኤው የዞኑን ህዝብ ምክር ቤት፣ አስተዳደር ምክር ቤትና ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2016 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2017 ዓ.ም ጠቋሚ ዕቅድ፣ የ2017 በጀት አመት ረቂቅ የበጀት አዋጅ እና ልዩ ልዩ ሹመቶች ቀርበው ውይይት ከተደረገ በኋላ እንደሚጸድቅ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።
በጉባኤው የክልልና የዞን ምክር ቤት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በቅንጅትና በጥምረት መስራት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ
አካባቢን በመጠበቅና በማጽዳት ምቹና ጽዱ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሁሉም የድርሻውን ልወጣ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳሰቡ
ግለሰባዊ ነጠላ ትርክቶችን በጋራ በመታገል በመደመር እሳቤ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ