በሀገረ-መንግስት እና በሰላም ግንባታ ስራዎች የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት 2ኛ አመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤ የ2016 እቅድ ክንውን እና የ2017 ጠቋሚ እቅድ በማጽደቅ ተጠናቋል።
የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት በክልሉ የሚገኙ 13 ነባር ብሔረሰቦች ውክልና የተሰጣቸው አባላቶቻቸው በምክር ቤቱ የሚከናወኑ ተግባራትን እንደሚከታተሉና እንደሚገመግሙ የተመላከተ ሲሆን፥ የምክር ቤቱ 2016 የአፈጻጸም ሪፖርት በምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ በአቶ መሰለ ከበደ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
የምክር ቤቱ አባላትም በተለይ የክልሉን ህዝቦች ባህል፣ ቋንቋና ወግ ለማሳደግ በተሰራው ስራ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።
በክልሉ ባሉ ሁለት ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች በስምንት ቋንቋቸውን ተተርጉሞ ባህላቸውንና ታሪካቸውን የማስተዋወቅ ተግባራት መከናወኑ በጥሩ ተግባር የተገመገመ ሲሆን፥ ይኸው ተግባርም በሌሎች ቋንቋዎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ከሰላም ግንባታ አንጻር በክልላችን ከወትሮ በተሻለ ሁኔታ ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ አንዳንድ ጥፋቶች እየታረሙ የመጡበት ሁኔታ መኖሩን የገለጹት የምክር ቤት አባላቱ፥ በተለይ በህዝብ ውስጥ ያደሩ ቅራኔዎችን በንግግር እና በሰላማዊ ሁኔታ ለመፍታት የተሄደበት መንገድ ጥሩ በመሆኑ ውጤት ተገኝቶበታልም ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በተለይም ከፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት ጋር ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተም ባደረጉት ግምገማም ህዝቡ በእጁ ያለውን ሀብት በተገቢው ከመጠቀም አንጻር የነበሩ ውስንነቶች ተቀርፈው በተገቢው ጥቅም ላይ እንዲውሉ መደረግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
ከመንግስት የሚወርዱ በጀቶች በተለይም ከቀመር አንጻር በ1999 የተደረገ የህዝብ ቆጠራ ቀመር አሁን ካለው የህዝብ ቁጥር አንጻር ልዩነት ያለው በመሆኑ ተገቢ መረጃ በመያዝ ቀመሩ የሚስተካከልበት መንገድ ከፌደሬሽን ምክር ቤት ጋር በመነጋገር ሊስተካከል ይገባልም ብለዋል።
ባህላዊ የዳኝነት እና የእርቅ ስረአቶች ለሰላም ግንባታው ወሳኝ ነው ያሉት የምክር ቤት አባላት ይኸው ተገባር ተጠናክሮ መሰራት ይገባዋል ብለዋል።
በጉባኤው ላይ የተገኙት የምክር ቤቱ አባል እና የክልሉ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወሰነች ቶማስ በበኩላቸው፥ ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሰላም ግንባታ ዙሪያ በሰራው ስራ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።
ምክር ቤቱ የክልሉ ቀመር ጉዳይ በስፋት ማንሳታቸው ትክክል መሆኑን አውስተው በቀጣይ ከፌደሬሽን ምክር ቤት ጋር በመነጋገር በቀመሩ መሰረት ሀብቱ እኩል የሚከፋፈልበት ሁኔታ እንዲኖር ይሰራል ብለዋል።
የደቡብ ምእራብ ህዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤው አቶ መቱ አኮ በበኩላቸው በሰላም እሴት ግንባታ እና በፌደራሊዝም ስረአት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በክልሉ ባሉ ኤፍ ኤም የተጀመሩ ተግባራት በክልሉ ባሉ አራት ኤፍ ኤሞች በሁሉም ቋንቋ ተደራሽ ይሆናል ብለዋል።
ከበጀት ቀመር ስራ ጋር በተያያዘ መረጃ የማጥራት እና የልምድ ልውውጥ ስራ በቀጣይ ተጠናክሮ ይሰራልም ብለዋል።
ምክር ቤቱ ቀደም ሲል ያካሄደውን የምክር ቤቱን የ2ኛ አመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ መርምሮ ያጸደቀ ሲሆን፥ የ2016 የምክር ቤቱን እቅድ ክንውን ሪፖርት፣ ቃለጉባኤ እና የ2017 እቅድ ምክር ቤቱ በስፋት ከተወያየበት በኋላ አጽድቋል።
ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ