የኮሬ ዞን ከፌዴራልና ከክልል የህዝብ ተወካዮች ጋር ውይይት ማድረግ ጀመረ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኮሬ ዞን ምክር ቤት ከፌዴራልና ከክልል የህዝብ ተወካዮች ጋር የህዝብ ለህዝብ ውይይት በማካሔድ ላይ ናቸው፡፡

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኮሬ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈጉባዔ አካላት በቀለ፥ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የመልማት ጥያቄዎችና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ደረጃ በጀረጃ ከወረዳ እስከ ፌደራል ቀርበው ምላሽ ያገኛሉ ብለዋል።

በኢፌዲሪ የኮሬ ህዝብ ተወካይ አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ህግ ምርጫ ከተደረገ በኋላ የህዝቡ ተወካዮች በዓመት ሁለት ጊዜ ውይይት በሚያደርጉት መሠረት ባለፈው የካቲት አወያይተው እንደ ነበር በማስታወስ የአሁኑን በየቀበሌያቸው በማወያየት የህዝቡን ጥያቄ በመለየት ባለቤቱን አግኝቶ በወረዳና በክልል ደረጃ የማይፈቱ ጥያቄዎች አስከ ፌዴራል ቀርበው እንዲፈቱ አቅጣጫ እንደተቀመጠ ተናግረዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኮሬ ዞን ተወካይ ዜናነህ አዱላ (ኢ/ር)  በተጀመረው ውይይት በሁለም ዘርፍ ክፍተቶችን በመለየት ለግምገማ ከራሳችን በመነሳት ህዝብና መንግሥት ድርሻውን እንዲወጣ የህዝብ ለህዝብ ውይይት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አስጨናቂ ጆንቴ፣ ስለሺ ስንቦና ሌሎችም የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመብራት፣ የጤና አገልግሎትና ዓመታትን ባስቆጠረ የፀጥታ ችግር ቆላማ ቀበሌያት መሬት ያለማልማት፣ በመንገድ መዘጋት ህብረተሰቡ ለእንግልት እየተዳረገ እንደሚገኝ በመግለጽ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ዘጋቢ: ምርጫ መላኩ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን