የባልቻ ገዳም

በመሐሪ አድነው

በ1854 ዓ.ም የተወለዱት ባልቻ ሳፎ /አባ ነፍሶ/ በአፄ ምኒልክ ጦር ተማርከው ነበር ወደ ምኒልክ ቤተመንግስት የገቡት። ምኒልክ የማረኩትን ከማስጨነቅ ይልቅ በእንክብካቤ መያዝና ማስተማር ይቀናቸዋልና ታዛዥና ታማኝ ሆነው ያገኟቸውን ባልቻን በግምጃ ቤታቸው እንዲሰለጥኑ አደረጓቸው፡፡ ባልቻም በጥረታቸው ከባጅሮንድነት ተነስተው እስከ ደጃዝማችነት ማእረግ ደረሱ፡፡ በአድዋ ዘመቻ ተሳትፈው በመድፍ ተኳሽነታቸውና በጀግንነታቸው ስለታወቁ “ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ” ተብሎ ተገጠመላቸው፡፡ ከአደዋ ጦርነት በኋላ ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ በተለያየ ጊዜ በቀድሞ አጠራር ሲዳሞ ክፍለ ሀገር፣ ሐረርጌንና ባሌን አስተዳድረዋል። በሰገሌ ጦርነት ወቅትም ከተማ ጠባቂ ተብለው ተሹመው አዲስ አበባን አረጋግተው ቆይተዋል፡፡

ሲዳሞን ባስተዳደሩበት ወቅት የከፍለ ሃገሩ ዋና ከተማ የሆነችውን ሃገረ ሠላምን ቆረቆሩ፡፡

ሃገረ ሠላም ከተማ የተቆረቆረችው በ1909 ዓ.ም ነው፡፡ “ሀገረ ሠላም የባልቻ ገዳም” እያሉ ነው ነዋሪዎቿ የሚጠሯት፡፡

ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶን ተከትለው በሀገረ ሠላ የሠፈሩ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦ ይኖራሉ፡ እንደ ክ/ከተማ ሊቆጠር በሚችል መልኩ የተቀመጡ አራዳ እና መዓድን የሚባሉ ከተሞች ያሏት የሀገረ ሠላም ከተማ የተለያዩ መጠሪዎች ያላቸው ሠፈሮችም የከተማዋ መለያዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ጐንደር ሠፈር፣ ጉራጌ ሠፈር፣ ሽቆ ሠፈር፣ ቁጠባ ሠፈር፣ ጐጃም ሠፈር፣ ኮይራ ሠፈር፣ ወለጋ ሠፈር፣ ወሎ ሠፈር እና ፋኖ ሠፈር ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በቀድሞ አጠራር በሲዳሞ ክፍለ ሃገር ውስጥ ከነበሩት ወረዳዎች ሰፊ የቆዳ ስፋት አላቸው ከሚባሉት መካከል ሃገረ ሠላም አንዷ እንደነበረች ይነገራል፡፡

ወረዳው በአጠቃላይ 88 ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነበረው፡፡ የእነዚህ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ተወላጆች በሙሉ የተማሩት በደጃዝማች ባልቻ ት/ቤት ነው፡፡

ደጃዝማች ባልቻ ት/ቤት የተመሠረተው በ1939 ዓ.ም ነው፡፡ ት/ቤቱ በክፍለ ሃገሩ ቀደምት ከሚባሉት ውስጥ ይመደባል፡፡ በጣም ብዙ አቅም ያላቸው የሀገረ ሠላም ተወላጆች በመላው ዓለም ይገኛሉ፡፡ ምሁራኖችን፣ ሚንሰትሮችን፣ አምባሳደሮችን፣ ከፍተኛ የጦር መሪዎችን፣ እንደዚሁም በሀገራችን ካሉት ጥቂት ቢሊየነሮች ተርታ የሚመደቡ ባለሀብቶችን ያፈራ ት/ቤት ነው – ደጃዝማች ባልቻ ት/ቤት፡፡

ይህንን አቅም አሰባስቦ የትውልድ ሀገራቸውን ለማሳደግ በርካቶች በተለያየ ጊዜ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሆኖም ግን በሁኔታዎች አለመመቻቸት ምክንያት ሳይሳካ ቆይቷል፡፡

በሀገረ ሠላም ተወላጇ ዶ/ር ሣራ ፀጋው ሃሳብ አመንጭነት የብዙዎች ምኞች የነበረውን ሃሳብ ለማሳካት ጥቂት ሆነው በቴሌግራም የጀመሩት እንቅስቃሴ ብዙዎችን አሰባስቦ አሁን ላይ ወደ ማህበር ምስረታ ገብቷል፡፡

የማህበሩን ዓላማ በተመለከተ ዶ/ር ሣራ እንዳብራራችው በሶስት ዋና ዋና ነገሮች ላይ ያተኩራል፡፡ የማህበራዊ ጉዳይ የመጀመሪያው ሲሆን የተወላጆቹን የእርስ በርስ ግንኙነት የሚያጠናክርና ከማህበረሠቡ ጋር ያለውን ትስስር እንዲጨምር የሚያደርግ ነው፡፡ የበጎ አድራጐት ተግባር ሌላኛው ነው፡፡ በሀገረ ሠላም ከተማ የሚኖሩ የቀድሞ የደጃዝማች ባልቻ ት/ቤት መምህራንን ጨምሮ የአካባቢውን ማህበረሰብ መደገፍና የብዙዎች መፍለቂያ የሆነውን የደጃዝማች ባልቻ ትምህርት ቤትን በማዘመን አሁን ያለው ትውልድ የተሻለ ትምህርት አግኝቶ የፊተኞቹ ወደ ደረሱበት ደረጃ ማድረስ የሚችል የበጎ አድራጐት ዘርፍ ይኖራል፡፡ በዚህ የበጎ አድራጐት ዘርፍ ታዲያ ትውልዱ በእርዳታና በጠባቂነት ብቻ እንዳይቀጥል ማድረግ የሚያስችል የቢዝነስ ዘርፍ ተጨምሮበታል፡፡ ይህ ደግሞ ለተወላጆች የሥራ እድል በመፍጠር ለዘላቂ ለውጥ የሚያበቃ ነው ተብሏል፡፡

እንደ አጠቃላይ ማህበሩ 3 መቶ ቋሚ አባላት ሲኖሩት ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ ደጋፊ አባላትን ያቀፈ ነው፡፡

የእነዚህን ሁሉ አቅም አሰባስቦ አንድ ወጥ የሆነ የጋራ ተቋም ወይም አክሲዮን በማቋቋም ተቋሙ ራሱን ችሎ የሚቀጥልበትን እድል ማመቻቸት የሚያስችል ሲሆን አባላቱንም ሁልጊዜ የእርዳታ ገንዘብ አምጣ የሚባልበትን ሁኔታ ማስቀረት ያስችላል፡፡

የተወሰነ ገንዘብ አንድ ጊዜ አዋጥቶ ያን ብር ኢንቨስት የሚደረግበት እንጂ የሚባክን እንዳልሆነ እያንዳንዱ አባል አምኖ ይቀበላል። ከሚሠራበት የገንዘብ ትርፍ እያንዳንዱ አባል የአክሲዮን ድርሻ የሚኖረው ሲሆን ግማሹ ደግሞ ለበጎ አድራጐት ተግባር እንደሚውል ለማወቅ ተችሏል፡፡

አቶ ቡንቱቃ ዋሬ የሃገረ ሰላም ከተማ ተወላጅ ናቸው፡፡ ከቀደምት የደጃዝማች ባልቻ ት/ቤት ተማሪዎች መካከል አንዱ ናቸው አቶ ቡንቱቃ፡፡ ዘለግ ላለ ጊዜ በተማሩበት ት/ቤት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነውም ለረጅም አመታት አገልግለዋል፡፡ አሁን በህይወት ከሌሉት የሀገረ ሠላም ተወላጅ ከሆኑት ከቀድሞ የኢፌዴሪ ፍትህ ሚኒስትር አቶ ሃርቃ ሃሮዬ ጋር በመሆን የሀገረ ሠላም ተወላጆች ማህበር ለማቋቋም እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በተፈጠረ የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ሃሳባቸው ሳይሳካ በጅምር ቀርቋል፡፡ ለዘመናት ሲመኙት የነበረው የሀገረ ሠላም ተወላጆች ማህበር ምስረታ አሁን ላይ በልጆቻቸው እውን ስለሆነ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው በእለቱ ገልፀዋል፡፡

ከሀገረ ሠላም ከወጡ ብዙ ጊዜ እንደሆናቸው የሚናገሩት ኮ/ል በርሃኑ ነጋሽ የትውልድ ሀገራቸውን ተመልሰው መደገፍ ባለመቻላቸው ቁጭት ይሰማቸው ነበር። ዛሬ ላይ ግን ይህ እድል በመፈጠሩ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ እውቀት ያለው በእውቀቱ ያሳደጋቸውን ማህበረሠብ ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል፡፡

ኢንጂነር መሳይ ማቱሳላ በበኩሉ ሀገረ ሠላም የኢትዮጵያ ምሳሌ ናት ይላል፡፡ የተለያየ ብሄረሰብ የተለያየ ቋንቋና የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ሠዎች ያለ ልዩነት በፍቅርና በመተሳሰብ የሚኖሩባት ከተማ ነች ሀገረ ሠላም፡፡

በመሆኑም የሀገረ ሠላም ትዝታው ሁሌም ከአእምሮው እንደማይጠፋ ይናገራል፡፡ ማህበሩ አንጋፋዎቹንና የአሁን ትውልድን ያቀፈ በመሆኑ ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚችል እንደሆነ ሙሉ እምነት አለው፡፡

ላለንበት ደረጃ ለመድረሳችን፥ የሀገረ ሠላም ከተማ ነው መነሻችን፡፡ የቀደሙት የሀገረ ሠላም ነዋሪዎች ያሳዩንን የአንድነት መንገድ ተከትለን ነው ዛሬም ድረስ የዘር፣ የብሄር፣ የቋንቋና የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድበን ተሰባስበን ይህን ማህበር መመስረት መቻላችን፡፡ ለሌላው የኢትዮጵያ ክፍል መልካም አርአያ ሲሆን የሚችል ነው የሚለው ደግሞ አቶ ጆርጅ ሃንቃሎ ነው፡፡

ሁላችንም አንድ አንድ መፅሐፍ ለተማርንበት ደጃዝማች ባልቻ ትምህርት ቤት ብናዋጣ በትንሹ አንድ ሺህ መፅሐፍት ለቤተመፅሐፍቱ በአንድ ጊዜ ማበርከት አንችላለንና ቀዳሚው የበጐ አድራጐት ሥራችን የሚሆነው እርሱ ነው በማለት ነው አቶ ጆርጅ ሃነቃሎ ሃሳቡን ያጋራው፡፡

ይህ ጥብቅ ትስስር የፈጠረው ህብረትና አንድነት በዘመኑ በነበረውና ሃላፊነት በሚሠማው ትውልድ ላይ አርፏልና ዛሬ ደግሞ ተሰባስቦ የኖረበትንና ያደገበትን አካባቢ ለማስታወስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

የሀገረ ሠላምና አካባቢው ልጆች ማህበር በትንሽ አባላት ተጀምሮ ብሄር፣ እድሜ ፆታ ሳይመርጥ ገና ከጅምሩ በርካታ አባላተን ማፍራት የቻለው ይህ ማህበር በቀጣይ ጉዞው የሚሰምር ውጤት እንደሚያከናውን የብዙዎች እምነት ሆኗል፡፡

ለቀጣዮቹ ወቅቶች ራዕዮን ይፋ በማድረግ በአደባባይ የተመሠረተው የሀገረ ሠላም ልጆች ማህበራዊ ግሩፕን በምህፃሩ “ሀልሶንግ”ንብዙዎች ይደግፋሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

የሀገረ ሠላምና አካባቢው ልጆች ማህበር መመስረት ዋነኛ ዓላማው የጋራ አንድነትን በመፍጠር ችግሮችን በጋራ ለመቅረፍ የሚያስችል አቅም መገንባትና መፍጠር መሆኑ በግልፅ ተቀምጧል፡፡

ዶ/ር ሣራ ፀጋው እንዳስረዳችው ማህበሩ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ አለው፡፡ በቢዝነሱ ዘርፍ የአባላቱን ኑሮ ማሻሻል የሚቻልበትን የቁጠባና ብድር ተቋም መመስረት ቀዳሚ ተግባር እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ እቅድ ከሚተገበሩት መካከል በተለይም ሐዋሣ ላይ ያልተለመደውን የሪልስቴት ቢዝነስ ለመጀመር የሚያስችል ጥናት ተጠናቋል፡፡

በማህበራዊ ዘርፉ ደግሞ አባላት በአመት አንዴ ወይም ሁለት ጊዜ እየተገናኙ ማህበራዊ ተስስራቸውን የሚያጠናክሩበት፣ የሚወያዩበትና የሚመካከሩበትን መድረክ ማዘጋጀትና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡

በቴሌግራም ተጀምሮ ሁሉንም እቅድና ሃሳብ በ”ኦንላይን” ውይይት አጠናቆና በአካል ተሰባስቦ በሐዋሣ ከተማ በይፋ የተመሠረተው የሀገረ ሠላምና አካባቢው ተወላጆች ማህበራዊ “ሀልሶግ” ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባት የሚያስከትለውን ህጋዊ ፍቃድና እውቅና ማግኘት መቻሉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡