የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2017 ዕቅድ ዙሪያ ከቢሮው ማናጅመንት አባላት እና ባለሙያዎች ጋር በዲላ ከተማ ውይይት መድረክ አካሂዷል።

የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ዘብዲዎስ ኤካ፤ የውይይት መድረኩን በንግግር በከፈቱበት ወቅት በ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀም በጥንካሬ የተለዩና በውስንነት የተገመገሙ ጉዳዮች የመፍትሄ አቅጣጫ ለመዘርጋት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መድረክ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቀነስ የመንጃ ፍቃድ አሰጣጥ ዘመናዊና በሶፍትዌር የታገዘ በማድረግ በቀድሞ የደቡብ ክልል የተጀመረውን ታርጋ የመቀየር ሥራ መጀመራቸውንም ተናግረዋል፡፡

የቢሮው ምክትልና የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተገኘ ግርማ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የትራፊክ አደጋ ምክንያቶችን በመለየት አደጋውን ለመቀነስ የሚረዱ ስልቶችን በመከተልና የአደጋውን አስከፊነት በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት እንዲካተት በማድረግ የግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የትራፊክ ጉዳይ የፖሊስና የትራንስፖርትና መንገዶች ልማት ቢሮ ጉዳይ ተደርጎ ይታይ የነበረውን ግንዛቤ በመቀየር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በዘርፉ እየታየ ያለውን አስክፊ አደጋዎችን ለመቀነስ እየተሠራ እንደሆነም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

በመንገዶችና ትራንስፖርት ልማት ቢሮ ምክትልና የገጠር ተደራሽ መንገድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መስፍን ስለሽ በዘርፉ በተከናወኑ ሥራዎች አመርቂ ውጤት መታየቱን ገልጸው በተለይም በህብረተሰብ ተሳትፎ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተቋሙ የሚስተዋለውን የሎጀስቲክ አቅርቦት ችግሮችን በመቅረፍ በተያዘው በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ ማናጅመንት አባላት እና ባለሙያዎች ባለፈው በጀት ዓመት በቢሮ ደረጃ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው ለዚህም የበኩላቸውን እንደተወጡ ተናግረዋል።

በቀጣይም በ2017 በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፎች ቅንጅታዊ ሥርዓት በመዘርጋትና በመተጋገዝ ዕቅዱን ለማሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ በመግለጽ ቢሮው አስፈላጊውን የቁሳቁስና የሎጀስቲክ አቅርቦት ችግር እንዲቀርፍላቸው ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡ እምነት ሽፈራው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን