ወጣቶች ያላቸውን ጊዜ፣ እውቀትና ጉልበት በመጠቀም አቅመ ደካሞችንና የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍ እንዳለባቸው ተገለፀ

ወጣቶች ያላቸውን ጊዜ፣ እውቀትና ጉልበት በመጠቀም አቅመ ደካሞችንና የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍ እንዳለባቸው ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 24/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ወጣቶች ያላቸውን ጊዜ፣ እውቀትና ጉልበት በመጠቀም በክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች በንቃት በመሳተፍ አቅመ ደካሞችንና የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍ እንዳለባቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር ገለፀ፡፡

“በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የልዩ ወረዳዎች ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድአሚን በደዊ በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአእምሮ ከሚሰጠው እርካታና ለህሊና ከሚሰጠው ሰላም ባሻገር በየትኛውም የእምነት አስተምሮ የተወደደ ተግባር ነው።

በልዩ ወረዳው ወጣቶችንና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በተከናወኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመላክተዋል፡፡

በ2018 በጀት አመት በበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የነበሩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠልና ጉድለቶችን በማረም በቀጣይ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚገባም ዋና አስተዳዳሪው ገልፀዋል።

በተለይም የአቅመ ደካሞችን ቤት ከማደስና ከመገንባት እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች የታቀዱ ተግባራትን በተቀመጠላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ መረባረብ እንደሚገባ አቶ መሀመድአሚን ተናግረዋል፡፡

የልዩ ወረዳው ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ካፉ አረቦ፤ ወጣቶች ያላቸውን እምቅ አቅም ወደ ተግባር በመቀየር የማህበረሰቡን ሰላም፣ ዕድገትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ማዋል እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡

በተያዘው የክረምት ወራት ወጣቶች በ16ቱም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘርፎች በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የልዩ ወረዳው ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አብድልዋሀብ ኑረዲን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶች ማህበረሰቡንና ሀገራቸው ያለምንም የግል ጥቅምና ክፍያ በማገልገል ያላቸውን ፍቅር በተግባር የሚያሳዩበት መሆኑን ገልፀው ባለፉት የበጋ ወራት በልዩ ወረዳው በዘርፉ ያሳዩት አበርክቶ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

የክረምት ወቅት ለወጣቶች የእረፍት ወቅት ብቻ ሳይሆን ያላቸውን ጊዜ፣ ጉልበትና እውቀት ለማህበረሰብ የሚያገለግሉበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በተያዘው የክረምት ወራት በግብርና ልማት፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በችግኝ ተከላና እንክብካቤ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና ጥገና፣ የከተማ ጽዳትና ውበት፣ የደም ልገሳና የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በዋናነት የሚከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አቶ አብድልዋሀብ አስረድተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ቤት ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንና ወጣቱ በክረምት ወቅት እውቀቱንና ጉልበቱን በመጠቀም በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በትኩረት መስራት አለበት ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ወለላ ኤልያስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን