በኣሪ ዞን በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ1 ሺህ በላይ ቤቶች ለአረጋውያንና አቅመ ደካሞች አድሶና ገንብቶ ለማስረከብ እየተሠራ እንደሚገኝ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገለፁ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዚሁ አካል የሆነውን በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች በአንድ ቀን ተግባራዊ የሚደረግ የቤት ግንባታ መርሐ ግብር መካሄዱን ያስረዱት የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ፤ በክረምት ብቻ እንደዞን ከ1 ሺህ በላይ ቤቶችን ለማደስና ለመገንባት ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፤ ፓርቲው ሰው ተኮር ልማታዊ ሥራዎችን ለማከናወን ያቀደውን ዕቅድ ወደተግባር እየቀየረ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ሲሉም አቶ አብርሃም አስረድተዋል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ብሄራዊ አገልግሎት እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስፋፊያ መሪና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዐብይ ሀይለመለኮት፤ በጎ ፈቃድ ዘር፣ ቀለምና ሀይማኖት ሳይለይ የሚተገበር ነው ብለዋል።
አመራሩ ህዝቡን በሥራው እንዲሳተፍ በማስተባበር ሀላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት ሲሉም ገልፀዋል።
መንግስት ለተግባሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንዳለም አቶ ዐብይ ገልፀው፤ በየአካባቢው እየተሠራ ያለው ሥራ የሚያስደስት ነው ብለው ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትልና የወጣቶች ዘርፍ ሀላፊ አቶ ማርቆስ ማቴዎስ እንደገለጹት እንደክልል በክረምት ከ3 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት እየተሠራ ነው።
ወጣቶች በዚህ ሥራ በስፋት እየተሳተፉ መሆኑን ገልፀው ሁሉም የክልሉ ነዋሪ በበጎ ህሊና በበጎ ሥራው አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪ አቅርበዋል።
አስተዋጽኦ እያበረከቱ ላሉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
መርሐ ግብሩ የተጀመረባቸው የወረዳና የጂንካ ከተማ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች እንደዞን ከተያዘው ዕቅድ በላይ ለአቅመ ደካሞችና ለአረጋዊያን ቤት ገንብቶ ለመስጠት በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ጂንካ ከተማ አስተዳደር፣ ባካ ዳውላና ደቡብ አሪ መዋቅሮች የአንድ ቀን የቤት ግንባታ መርሐ ግብርን የፌደራል፣ የክልል፣ የዞን፣ የከተማ አስተዳደርና የወረዳ አመራሮች በተገኙበት አስጀምረዋል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ