በ2016 ዓ.ም በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በአንድ ጀንበር የሚገነቡ ቤቶች መርሐ ግብር 72 ቤቶች በኮሬ ዞን እየተሠሩ መሆናቸው ተገለጸ
የኮሬ ዞን ወጣቶች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ሳታና ሳዲሁን፤ በዞኑ 14 ዘርፎችን ያቀፈ ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው የአንድ ጀንበር መርሐ ግብር ከ72 በላይ ቤቶች እንደሚገነቡ አስረድተዋል።
የ2016 ዓ.ም የክረምት ፕሮግራም ከ87 ሺህ በላይ ወጣቶችና በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ 1መቶ 60 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥት ወጪ በመሸፈን 2 መቶ 28 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ አቅደው እየሠሩ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ለአቅመ ደካሞች ቤት መሥራት አንዱ ሲሆን ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች አቶ ሁሴን ጂሹዋዴ በኢኮኖሚ አቅም ማነስ በመኖሪያ ቤት እጦት ይቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል።
ከዶርባዴ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል ወ/ሮ ዘነበች እንዳለ ከስድስት ልጆቿ ጋር በማይመች ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ገልጸዋል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በተደረገላቸው በጎ ተግባር መደሰታቸውን ገልጸው በበጎ ሥራ የተሳተፉ ወጣቶችን የጎርካ ወረዳና የኮሬ ዞን አመራሮች አመስግነዋል።
በዞኑ የጎርካ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ታደሰ፤ በአንድ ጀምበር የሚገነቡ ቤቶች መርሐ ግብር በወረዳው 24 ቤቶች ግንባታ በይፋ መጀመሩን ተናግረዋል።
በክረምቱ በጎ ሥራ ከተሳተፉ ወጣቶች ደሳለኝ ደንእ እና ቸርነት ተሾመ፤ በጎ ተግባር ከሰውና ከፈጣሪ በረከት የሚያስገኝ የነገ ስንቅ በመሆኑ ሁሉም ወጣቶች ቢሳተፉበት መልካም ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ምርጫ መላኩ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
በ6 ወራት ውስጥ ሊመዘበር የነበረ ከ156 ሚሊየን 560ሺህ ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለጸ
የጉራጌ ክትፎ ባህልና እውቀትን በዩኒስኮ የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢፌዲሪ ቅርስ ባለስልጣን ገለፀ
በክልሉ ያሉ ብሔረሰቦችን ባህል ወደፊት በማውጣት የአካባቢውን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል በትኩረት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ተናገሩ