በመካሄድ ላይ ባለው የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ54 ሚልዮን ብር በላይ ለማዳን እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኦሞ ዞን በ2016 ዓመት ምህረት በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሚከናወኑ ተግባራት ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስትና ህዝብ ወጭ ለማዳን ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።

እስካሁን ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚገመት የበጎነት ተግባር መከናወኑንም መምሪያው አመላክቷል።

በዘንድሮው የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች፣ ኮሌጆች እንዲሁም የመንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑና የእምነት ተቋማትና የበጎ አድራጎት ማህበራትን በማሳተፍ በ15 የትኩረት መስኮች የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መመሪያ ኃላፊ አቶ ንጉሴ ማቴዎስ ገልፀዋል።

በክረምቱ ወራት በሚተገበሩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች 54 ሚልየን ብር የመንግስትን ወጪ ለማዳን ከታቀደው እስካሁን ከ20 ሚልየን ብር በላይ ወጪ የሚገመት ተግባር መፈፀሙን ያስረዱት ኃላፊው፤ በቀሪ ጌዜያት ሁሉም የዞኑ ወረዳዎችና ቱሪሚ ከተማ አስተዳደር በሀገር አቀፍ ለሚካሄደው የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ፣ የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና እድሳት ስራ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንዳለም አመላክተዋል።

በዞኑ የሐመር ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገሌ ሙዳ በበኩላቸው በክረምቱ ወራት በወረዳው 15 ሺ 1መቶ 3 ወጣቶችን በማሳተፍ 45 ሺ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በጎነት ድንበር የለውም ያሉት በወረዳው የኪንካ በጎ አድራጎት ወጣቶች ማህበር ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ዛንጋ ኛይቶ ማህበሩ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን በዞኑ እና አጎራባች ዞኖች እየሰራ እንዳለ ተናግረዋል።

ወጣት ኤርሚያስ ዶይማና ስንታየሁ ኑሩ በዘንድሮው የክረምት ወራት በአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ቤት ግንባታና እድሳት፣ በችግኝ ተከላ፣ በገቢ አሰባሰብና ህገወጥ ንግድ ቁጥጥር እና በሌሎች ዘርፎች ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን የተሣተፉባቸው የበጎነት ሥራዎች የህሊና እርካታን እንዳጎናጸፋቸውና ለቀሪ ስራዎችም መነሣሣትን እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።

ዘጋቢ: በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን