የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለፁ።

ከቅድመ 1ኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያለው ጥቅል ተሳትፎ እና ንጥር ተሳትፎ ለማሳደግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት እርብርብ የሚሻ መሆኑን አጽንኦት የሰጡት ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው፥ የትምህርት ተሳትፎ ከልዩ ፍላጎት፣ ከሴቶች፣ ከጎልማሶች እና ከመምህራንና ከትምህርት አመራር ሚና ላይ ያሉ ውስንነቶችን መቅረፍ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ትምህርት የፖለቲካ መሳሪያ ሳይሆን አገርና ትውልድን መገንቢያ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፥ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የተጀመሩ ጥረቶች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

የትምህርት ስራ ከሌሎች ስራዎች አንጻር ረዥም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ያመላከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በዘርፉ ስኬታማ ለመሆን የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

የኢፌዲሪ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው የመምህራንና የትምህርት ሴክተሩን ሪፎርም በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ወጥ የሆነ አገራዊ የትምህርት ሪፎርም እየተሠራ በመሆኑ አንዳንድ ጉዳዮች በዚያው ዘላቂ መፍትሄ ያገኛል ብለዋል።

የልጆቹን አካላዊ ብቃት ለማሳደግ የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር በማካሄድ ለተማሪዎች ሁለንተናዊ እድገት ድርሻ ያለው በመሆኑ በቀጣይ አመት ይጀመራል ብለዋል።

በመድረኩ የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ እና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።

ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ