ባህል የአንድ ህዝብ ማንነት መገለጫ እሴት ነው። ምንም እንኳ ባህል የምንለው እሴት አንድም ኃይማኖታዊ ሌላም ህዝባዊ መሠረት መያዛቸው ከዘመን ዘመን ሳይደበዝዙ ዛሬም ድረስ እንደ አከባበራቸው ባህርያት ሲከበሩ ቆይቷል። ከእነዚህ ኃይማኖታዊ በአላት መካከል አንዱ ቡሄ ነው።
ቡሄ ወይም የደብረ ታቦር በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በወርሃ ነሐሴ ቀን 13 የሚከበር በዓል መሆኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ይነገራል፡፡
ቡሄ በወርሃ ነሐሴ በፍልሰታ ፆም መባቻ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡
ቡሄ የራሱ የሆነ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ትርጓሜና አመክንዮም እንዳለው ይነገራል፤ ለክረምት ወራትም የራሱን ድባብ ችሮ ያሚያልፍ በዓል ጭምር ነው፡፡
የቀደሙ አባቶቻችን ቡሄን በክረምት ባሕር ላይ መሻገራችንን የሚያመላክተን የቂጣ ድልድይ አድርገው ይገልጹታል፡፡
የነሐሴን ቦይ መሻገራችንን የሚያረጋግጥ በዓል ነው እንዲሉ አባቶች ከቡሄ በዓል ጋር አያይዘውም “ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” በማለት በዓሉን በምሳሌ ያስረዳሉ፡፡
ያለንበት ወርሃ ነሐሴ እንደመሆኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች በዓሉን ታሳቢ አድርገው የሚከበሩ እንደ አሸንድዬ፣ አሸንዳና ሶለል የመሳሰሉ የልጃገረዶች ጨዋታ ከኃይማኖታዊ ስርአቱ ባለፈ ህዝባዊ መሠረት ይዘው ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገሩ ዛሬ ላይ ለመድረሳቸው ይነገራል።
ከደሬቴድ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሀዋሳ ደብረ ምጥማቅ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን አገልጋይ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ደረጄ ሚደቅሳ እንደሚገልጹት፤ በዓሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወህዶ እምነት ተከታዮች ከሚያከብሩት ከኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ መሆኑን ገልፀው፥ በዓሉ ደብረ ታቦር የሚለውን ስያሜ ያገኘው የስላሴ ሚስጢር ወይም የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ለሀዋርያቱ ከተገለጠበት ተራራ ጋር ተያይዞ የተሰጠ ስያሜ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የበዓሉ ሐይመኖታዊ አከባበር ስርዓቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፥ ከዘመናት መወራረስ በኋላ በሀገራችን እንደ ህዝባዊ በዓል በመከበሩ እንዲሁም ቡሄ የሚለውን ስያሜ የእምነቱ ተከታዮች ከልማድና ባህል ጋር አስተሳስረው የመለኮቱን መገለጥ ለመጠቆም የሰጡት ስያሜ እንደሆነ ይስረዳሉ፡፡
በአሉ የመገለጥ በዓል ተብሎ መጽሃፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለዉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሀዋርያቱ እስኪወድቁ አስደንጋጭ የነበረውን አብ ያሰማዉን ነጎድጓዳማ ድምፅና ብርሃነ መለኮቱ የተገለጠበትን ምሳሌ በማድረግ በበዓሉ ዕለትም እረኞች ጅራፍ በማጮህ፣ እናቶች ሙልሙል ዳቦ በማዘጋጀት እንዲሁም ችቦ በመለኮስ ታስቦ እንደሚከበር ያብራራሉ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በክርስቲያኖች ዘንድ ቆስጠንጥኒዮስ የሚባል ደገኛ በነገሰበት ዘመን 3ኛው መቶ ክ/ዘመን የተጀመረ ሲሆን በሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን በሚባሉ ሊቀ ጳጳስ ዘመን ተጀምሮ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ዘመን ተስፋፍቶ መከበር እንደተጀመረም ይናገራሉ፡፡
በዓሉ በልዩ ዓይነት ሁኔታ የሚከበር ሲሆን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት መገለጥ በማሳብ እንደየ አካባቢዉ የእምነቱ ተከታዮች ለበዓሉ የተለያየ ስያሜ እየሰጡ ባህሉንም ሃይማኖታዊ ይዘቱንም ጠብቆ እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡
አዘጋጅ፡ ብዙነሽ ዘውዱ
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ