በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ1ሺህ 592 ኪ.ሜ በላይ አዲስ መንገድ ከፈታና ጥገና ስራ መሰራቱን ተገለፀ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ1ሺህ 592 ኪ.ሜ በላይ አዲስ መንገድ ከፈታና ጥገና ስራ መሰራቱን ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ልማት ቢሮ የ2016/17 ዓ.ም በጀት አመት ዕቅድና አፈፃፀም መድረክ በሚዛን አማን ከተማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ እንደተናገሩት ትራንስፖርት ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ፖለቲካዊ እድገትና ልማት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

በዚህም ቢሮው በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ1ሺህ 592 ኪ.ሜ በላይ አዲስ መንገድ ከፈታና ጥገና ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በክልሉ በሚገኙ ዞኖች በህብረተሰብ ተሳትፎ ከ15 በላይ ድልድዮችን መገንባት የተቻለ ሲሆን ከ315ሚሊዮን 915ሺህ ብር በላይ በመሰብሰብ የገንዘብ ድጋፍ  ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በክልሉ የትራፊክ አደጋ እያደረሰ ያለውን ሞትና የአካል ጉዳት ለመቀነስ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ ነው ብለዋል።

በተለይ በክልሉ ባሉት የህዝብ ትራንስፖርት መነሀሪያዎች  ላይ ከስምሪት ጋር ተያይዞ የሚታዩትን ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም ዘርፉን ሁሉም አመራሮች መከታተልና መደገፍ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን እንደገለፁት በዞኑ በቀድሞው ክልል ተጀምረው ሳይጠናቀቁ የቀሩትን የረጂም ጊዜ የመንገድ ልማት ጥያቄዎች ህብረተሰቡን በማስተባበር መፍታት መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም የዞኑን ህዝብ በማስተባር በርካታ የመንገድና የድልድይ ግንባታ ስራዎችን በማጠናቀቅ ማስመረቅ መቻሉን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታን ጨምሮ የተለያዩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የዞንና የወረዳ የተለያዩ የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊዎች ሆነዋል።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን