ምርታማነትን የሚጨምሩ የግብርና ግብዓት አቅራቦት ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ ነው

ምርታማነትን የሚጨምሩ የግብርና ግብዓት አቅራቦት ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ ነው

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተያዘው የመኸር እርሻ ከ1ሺ 700 ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዎባ አሪ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

በበልጉ ቴክኖሎጂንና የግብርና ምክረ ሀሳብን ተቀብለው በማረስ የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን በወረዳው የዘመር፤ የዲራመር እና የቦይካ ቀበሌ አርሶ አደር ዳኜ  ኖፅን፣ ታሪኩ መርሳብ እና በሀሩ ዘገዬ ተናግረዋል፡፡

በተያዘው የመኸር እርሻ ከ6 እስከ 8 ጥማድ መሬት ደጋግመዉ በማረስ የግብርና ምክረ ሀሳብን በመከተል የጓሮ አትክልት እና የበቆሎ ሰብል ለመዝራት ዝግጁ መሆናቸዉን ገልፀዋል፡፡

የግብርና ባለሙያዎች በየጊዜው ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆናቸዉን ጠቁመዉ ከዝናቡ መብዛት ጋር ተያይዞ የተዘራዉ መሬት በውሃ ሊበላሽ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የዎባ አሪ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኤክስቴንሽን ባለሙያና ሆልቲ ካልቸር ሰብሎች ልማትና ጥበቃ አስተባባሪ አቶ ዳዊት ማርቆስ በበልጉ የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት ወደ የመኸር እርሻ መገባቱን ጠቁመው በምርት ዘመኑ 3ሺ 591 ሄክታር መሬት ለማረስ ታቅዶ እስካሁን 1 ሺ 784  ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዓይነቶች መሸፈኑን አረጋግጠዋል፡፡

ምርታማነትን ለመጨመር የሚረዱ እንደ ኤን.ፔ.ኤስ፤ ዩሪያ እና ምርጥ ዘር የመሳሰሉት ላይ የሚስተዋለውን የአቅራቦት ችግር ለመፍታት ከዞንና ክልል መዋቅሮች ጋር እየተሰራ እንዳለም አስተባባሪው አስረድተዋል፡፡

ዘጋቢ፡ መላኩ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን