የቀቤንሲናን ቋንቋ ለማልማትና ለማሳደግ የቋንቋው መምህራን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

የቀቤንሲናን ቋንቋ ለማልማትና ለማሳደግ የቋንቋው መምህራን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቀቤንሲናን ቋንቋ ለማልማትና ለማሳደግ እየተደረገ ባለው ጥረት የመምህራን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

ጽ/ቤቱ የቀቤንሲና ቋንቋ የትምህርት አሰጣጥ ከሳባ ወደ ላቲን መቀየሩን ተከትሎ በቋንቋው የፊደል ገበታና የአፃፃፍ ዘይቤ ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ለመምህራንና ለዘርፉ ባለድርሻ አካላት ሰጥቷል፡፡

የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ አብድልመናን ሁሴን በሰጡት ማብራሪያ ከዚህ በፊት በቋንቋው ለመፃፍና ለማስተማር ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው የሳባ ፊደል አፃፃፍ ወደ ላቲን በመቀየሩ ሂደቱን በተመለከተ ለመምህራንና ለዘርፉ ባለሙዎች ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ስልጠናውን መስጠት ያስፈለገው ብለዋል፡፡

ቋንቋውን ለማልማት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን የገለፁት ምክትል ሀላፊው ሂደቱ ውጤታማ ሆኖ የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዲደርስ የቋንቋው መምህራን ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

ቋንቋውን ለማሳደግ ከተሰሩ መልካም ተግባራት መካከል በቅርቡ በዋቻሞ ዩንቨርሲቲ አማካኝነት ተጠንቶ ተግባር ላይ የዋለው የቋንቋ ማበልፀጊያ ድረ-ገፅ ቋንቋውን ለማልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ያወሱት አቶ አብድልመናን በሂደቱ ለተሳተፉ መምህራንና ለተቋሙ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በትምህርት ጽ/ቤቱ የስርዓተ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ሪባቶ ናስር በበኩላቸው የቀቤንሲና ቋንቋ አፃፃፍ ከሳባ ወደ ላቲን መቀየሩ መምህራንና ተማሪዎች በቋንቋው በአግባቡ ማንበብና መፃፍ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

ቋንቋውን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ከቴክኖሎጂ ጋር ማስተዋወቁ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት ያሉት አቶ ሪባቶ መምህራን ለቋንቋው እድገት ያላቸውን ሚና በመረዳት በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡን የቋንቋው መምህራንም የስልጠና መድረኩ በመማር ማስተማር ሂደቱ ያለባቸውን የክህሎት ክፍተት ለመቅረፍና የተሻለ ግንዛቤ እንዲጨብጡ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት በቋንቋው ለማስተማር ሲጠቀሙበት የነበረው የሳባ ፊደል አፃፃፍ ስልት ወደ ላቲን በመቀየሩ ሲያጋጥማቸው የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍና ተማሪዎችን በአግባቡ ለማብቃት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርላቸው መምህራኑ ገልፀዋል፡፡

ዘጋቢ፡ አስቻለው ተስፋዬ – ከወልቂጤ ጣቢያችን