በየአከባቢው ለሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ    

በየአከባቢው ለሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ                     

ሀዋሳ፤ ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በየአካባቢዉ እየተከሰቱ ባሉ የተፈጥሮ አደጋዎች መንግስት ተጎጂዎችን ለመታደግ እያደረገ ያለዉ ጥረት ለወገን ደራሽነቱን ያሳያል ሲሉ በአሪ ዞን ሰሜን አሪ ወረዳ የተጎጂ ቤተሰብ ተናገሩ።

በአሪ ዞን ሰሜን አሪ ወረዳ በአራት ቀበሌያት ያጋጠመው የመሬት መንሸራተት አደጋ ሞትና መፈናቀል አስከትሎ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ከግማሽ ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የአልባሳት፣ የመኝታ፣ የምግብና መሠል ቁሳቁሶችን በወረዳው በመገኘት ለወረዳው አስተዳደር እና ለተጎጂ ህብረተሰብ ተወካዮች ያስረከቡት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሐም አታ ናቸው፡፡

እርዳታውን የተረከቡት የሰሜን አሪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደግፌ ጌታቸው እንደወረዳ ተጎጂዎችን ለመታደግ ጉዳቱ ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰዉ የአሪ ዞን አስተዳደርና ልዑካን ቡድኑ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በእርዳታ ርክክቡ ከተገኙት የወረዳው ሀገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች መካከል  ቀሲስ ጌታቸዉ ፋንታዬ እና አቶ መልካሙ የክሞ የተፈጥሮ አደጋ ሰዉ ባልጠበቀውና በድንገት የሚከሰት በመሆኑ አደጋዉ በወረዳው በተከሰተዉ አደጋ ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመታደግ ዞኑ መንግስት ያበረከተዉ ድጋፍ የሚመሰገንና በርግጥም መሪው ፓርቲ ከቃል ባለፈ ሰው ተኮር ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

በርክክብ ስነ-ስረዓቱ ላይ የተገኙት የአሪ ዞን ብልፅግና ፓርት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የዞኑ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ በየአካባቢዉ እየተከሰቱ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች የዜጎችን ህልዉና የሚፈታተኑ በመሆናቸዉ እርስ በዕርስ የመረዳዳት ባህልን ከመቸውም ጊዜ በላይ ይበልጥ ማጠናከር ያስፈልጋል፤ መንግስትም ለህዝቡ ችግር ለመድረስ የሚያደርገዉን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ በዞኑ የሰሜን አሪ ወረዳን ጨምሮ በሌሎች ወረዳዎች ብሎም በክልሉና በሀገር አቀፍ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰተ ባለው የተፈጥሮ አደጋ እጅግ ማዘናቸውን ገልፀው ዞኑ አቅም በፈቀደ መጠን ለተጎጂዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ወንድማገኝ በቀለ – ከጂንካ ጣቢያችን