የሀገር ባለውለታ የሆኑት አረጋውያንን መደገፍና ማገዝ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሀገር ባለውለታ የሆኑ አረጋውያንን መደገፍና ማገዝ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ፡፡

የጉራጌ ዞን አረጋዊያን ማህበር አመታዊ ጉበኤ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል፡፡

የጉራጌ ዞን አረጋዊያን ማህበር አመታዊ ጉበኤው በወልቂጤ ከተማ ባካሄደበት ወቅት የተገኙት የዞኑ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ አቶ መኩሪያው ተመስገን እንዳሉት የሃገር አለኝታና ባለውለታ የሆኑት አረጋውያን መደገፍና መንከባከብ ይገባል፡፡

መምሪያው በ2016 በጀት ዓመት ለ683 ጠዋሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያን የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጉን አብራርተዋል፡

ለ1ሺህ 508 አረጋውያን የነፃ ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን የተናገሩት አቶ መኩሪያው በጉራጌ ዞን አረጋዊያን ማህበር ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማሳደግ ብር 616 ሺ ብር ድጋፍ ማድረጉን አክለዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበረሰቡን በማስተባበር 40 አዳዲስ ቤቶች ግንባታና የ19 ቤቶች ጥገና የተከናወነ ሲሆን ይህም በገነንዘብ ሲተመን 2 ሚሊየን 786 ሺህ 593 ብር መሆኑ ገልፀዋል፡፡

መምሪያው በቀጣይም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያንን የመደገፍ ተግባሩ አጠናክሮ እንደሚቀጥና አረጋግጠዋል፡፡

የጉራጌ ዞን አረጋውያን ማህበር ሰብሳቢ አቶ ተማም ሸሪፍ የማህበሩ አላማ የአረጋውያንን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሻሻል እንደሆነ ጠቁመው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከመንግስት በተገኘው በጀት በቀበሌ ደረጃ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አገራውያን መረዳት መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ውይይት በማድረግ አረጋውያንን ለመርዳት አጠናክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ደንድር ብሩ እና አቶ ትግስቱ ብርሳዊ በሰጡት አስተያየት ጧሪና አጋፊ የሌላቸው አረጋውያንን በመለየት ከወረዳና ከዞን መንግስት በተገኘ በጀት የተለያዩ ድጋፎች እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

ዘጋቢ ፡  እቴነሽ ቴሬቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን