የአፈር አሲዳማነትን ችግር በምርምር በመቅረፍ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየሰራሁ ነው – የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 09/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአፈር አሲዳማነትን ችግር በምርምር በመቅረፍ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡

ማዕከሉ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በቤንች ሸኮ ዞን ሼይ ቤንች ወረዳ ከ2 ቀበሌዎች ለተውጣጡ 40 ሞዴል አርሶ አደሮች በአፈር አሲዳማነት መከላከል ዘዴ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በክልሉ ግብርና ቢሮ የአፈር አሲዳማነት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ስር የሰው ሰራሸ ማዳበሪያ ባለሞያ ወ/ሮ ሙሉዓለም ክፍሌ ለግብርና ምርታማነት ማነቆ ከሆኑት መካከል የአፈር አሲዳማነት አንዱ መሆኑን ገልጸው የክልሉ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ ነዉ ብለዋል፡፡

በማዕከሉ የተፈጥሮ ሀብት ምርምር ዳይሬክቶሬት ተወካይ ወ/ሮ ቆንጅት አብረሃም እንደ ሀገር የአፈር ለምነትን የማሻሻል ስራዎች የተለያዩ ምርምሮች በማስደገፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ፣ ቨርሚ ኮምፖስት፣ ባዮሬድ እና ኖራን ተጠቅሞ የአፈር አሲዳማነትን በመከላከል ምርታማነቱን እንዲያረጋግጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ 44 በመቶ የእርሻ መሬት በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በማዕከሉ የአፈር አሲዳማነት ተመራማሪ አቶ በላይ ታደሰ ናቸው፡፡

በዚህም ክልሉ 8 መቶ 63 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

በሼይ ቤንች ወረዳ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽ/ቤት የተፈጥሮ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ዘማች  ኪዳኔ 96 በመቶ የወረዳው መሬት በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም አርሶ አደሩ ማዕከሉ ያመጣውን አዳዲስ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ጠይቀዋል፡፡

አርሶ አደር ኮይና ኮይስቲ፣ አትርሴ ገነራሻ፣ ፋንታሁን ፈረስና ሌሎችም በሰጡት አስተያየት መሬታቸው በአፈር አሲዳማነት በመጠቃቱ ምርት መስጠት ማቆሙን ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ ያመጣውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በመረሃ ግብሩ አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሞያዎች፣ የወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የስራ ሀላፊዎች፣ የቀበሌ ስራ አስኪያጆችና ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ ጫካ – ከቦንጋ ጣቢያችን