በታችኛው እርከኖች በሚገኙ ምክር ቤቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ጉባዔዎች እንዲካሄዱ ለማስቻል የተቀናጀ ጥረትን እንደሚፈልግ የዳዉሮ ዞን ምክር ቤት አሳሰበ

ሀዋሳ፡ 07/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዳዉሮ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 11ኛ የሥራ ዘመን 25ኛ መደበኛ ጉባዔ እያካሄደ ይገኛል።

በዞኑ ምክር ቤት ጉባዔ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ዳዊት ሚኖታ  በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች የሕዝብ ሉዑላዊነት መገለጫና ቀጥተኛ የሕዝብ ውክልና ይዘው የሚሠሩ ናቸው።

በመሆኑም ምክር ቤቶች በተሰጣቸው ኃላፊነት ተግባራቸውን ሕግና ሥርዓት ባለው ሁኔታ እንዲሠሩ የተቀናጀ ጥረትን ይጠይቃልም ብለዋል።

የዞኑ ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን የአስፈጻሚዎችን ዕቅድ አፈጻጸም በመገምገም ለሕዝቡ ለውጥና ዕድገት እንዲሁም ለውጤታማነት እየሠራ እንዳለ በመጠቆም።

በመሆኑም ዞኑን ባጋጠመው የበጀት እጥረትና በሌሎችም ምክንያቶች አልፎ አልፎ በአንዳንድ ወረዳዎችና ቀበሌያት ከአስቸኳይ ጉባዔ ውጪ መደበኛ ጉባዔዎች እየተካሄዱ አለመሆናቸውን አብራርተዋል።

ስለሆነም በቀጣይ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ለውጤታማነትና ለሕዝብ ሁለተናዊ ተጠቃሚነት በተቀናጀ ጥረት ሊሠራ እንደሚገባም አብራርተዋል።

ጉባዔው ያለፈውን ዓመት ጉባዔ ቃለ ጉባዔ፣ የ2017 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድና የሥራ ዘመኑን የበጀት ረቂቅ አዋጅና መግለጫ፣ የዳዉሮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዕቅድ አፈጻጸም፣ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ፣ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ማሟያ ምርጫና የዞኑ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ሹመት መርምሮ እንደሚያጸድቅ የምክር ቤቱ መርሀግብር ያመለክታል

ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ- ከዋካ ቅርንጫፍ