ሀዋሳ፡ ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሆሣዕና ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ምርት የሚደብቁና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን የመቆጣጠርና እርምጃ የመውሰድ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል።
በሆሳዕና ከተማ በሸቀጣ ሸቀጥ ድርጅት ሰራተኛ ሳለዲን ሻፊ በሰጠን አስተያየት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በንግድ ሥራ ላይ የተስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውን አልሸሸጉም፡፡ ይሁንና የመንግስት ቁጥጥር ሲደረግ የምርት ዋጋ ወደነበረበት ተመልሶ ተጨማሪ ምርት በማስገባት የተረጋጋ ንግድ ስለመቀጠሉ ተናግረዋል፡፡
ምርት ማከማቸትና መደበቅ ሸማቹን ከማጉላላትና ኑሮውን ከማዛባት ባለፈ ቸርቻሪውን ነጋዴ ይጎዳል የሚለው ሳለዲን ጅምላ አቅራቢዎች ጋር ያለው ጉድለት ከተስተካከለ የቸርቻሪውና የሸማቹም ችግር መፍትሄ ያገኛልና ትኩረት ቢደረግበት ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ከዚሁ የሸቀጣ ሸቀጥ ድርጅት ግብይት ሲፈጽሙ አግኝተን ያነጋገርናቸው ሸማቾች በሰጡን አስተያየት በከተማው ህግና ስርዓቱን ጠብቀው የሚሸጡ ነጋዴዎች እንዳሉ ሁሉ አላስፈላጊ ጭማሪ የሚያደርጉና ምርት የሚደብቁ በርካታ ነጋዴዎች ስለመኖራቸው አንስተዋል።
በመሆኑም መንግስት ህጉንና ስርዓቱን የተከተለ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግ ጠይቀዋል
ማህበረሰቡም ቢሆን ችግሮች ሲኖሩ የተቀመጡ የጥቆማ መስጫ አማራጮችን በመጠቀም ህገወጥነትን በጋራ መከላከል እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የሆሣዕና ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍስሃ ታደሰ በበኩላቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ምርት አከማችተው በሚደብቁና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሸማቹ ላይ የኑሮ ጫና የሚፈጥሩ ነጋዴዎችን የመቆጣጠርና እርምጃ የመውሰድ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በተቋቋመው ግብረ ሃይል አማካይነት እስካሁን በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ምርት አከማችተው በተገኙና ከዋጋ ዝርዝር ወጪ ስሸጡ በነበሩ 1መቶ29 የንግድ ተቋማት ላይ የእስርና የገንዘብ ቅጣትን ጨምሮ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱንም አቶ ፍስሃ አስረድተዋል፡፡
በከተማው እየቀረቡ ያሉ የፋብሪካና የኢንዱስትሪ ምርቶች በቂ ናቸው የሚል ድምዳሜ የለንምብለዋል፡፡ ለዚህም ጅምላ አከፋፋዮች ምርት በቀጥታ የሚያስገቡበት ሁኔታ ለማመቻቸት ከዞንና ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ስለመሆኑ ሀላፊው ገልጸዋል።
በተለይ የዘይት ምርትን ከአዳማና ከአዲስ አበባ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን በማከል።
በከተማ አስተዳደሩ የሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የግብረ ሃይሉ አባል አቶ ደግነት ሀይሌ በጉዳዩ በሰጡት አስተያየት በዚህ ወቅት በከተማው በአንዳንድ ህገወጥ ነጋዴዎች በሚፈጠሩ አሻጥሮች ህዝቡ እንዳይጎዳ ህግ የማስከበሩን ስራ በጋራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በከተማው በስድስቱም ቀበሌያት የፀጥታ አካላትን በመመደብ ህገወጥነትን የመከላከሉ ስርአት ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት አቶ ደግነት ህጋዊነትን ማስፈን በጸጥታ አካላት ብቻ ውጤታማ ሊሆን ስለማይችል በንግዱም ሆነ በፀጥታ ጉዳይ የሚፈጠሩ ህገወጥ ተግባራት ሲኖሩ ህዝቡ አፋጣኝ ጥቆማ እንዲሰጥ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል- ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ