በክልሉ በአመቱ በተቀናጀ የጤና አገልግሎት ዘርፎች ላይ የአፈፃፀም ግምገማና ለተመዘገበው አበረታች ውጤት ለባለድርሻ አካላት እውቅና የመስጠት ፕሮግራም በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
የጤና ልማት ስራዎችን በተገቢው በመተግበር የህብረተሰቡን ጤና ለማጎልበት ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ በየደረጃው ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ ገልፀዋል።
በክልሉ በዋና ዋና የጤና ዘርፎች በተቀናጀ የጤና ልማት ዘመቻ ማለትም በኩፍኝ ክትባት፣ የቤት ለቤት ፖሊዮ ክትባት፣ በስርዓተ ምግብ፣ በእናቶችና ህፃናት ጤናና ሌሎች መደበኛ ክትባቶች ላይ በአመቱ በርካታ ተግባራትን ማከናወን መቻሉንም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።
የክትባት ዘመቻ ተግባር እንደ ክልልና ሀገር 47 አመታትን ያህል ያስቆጠረ ተግባር ቢሆንም በዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ውጤትና ለውጥ ማምጣት ሳይቻል መቆየቱን የጠቆሙት አቶ አሸናፊ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረትና ርብርብ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
ክትባት ለህፃናት ሁለንተናዊ ጤናና እድገት ካለው ዘርፈ ብዙ ሚና ባሻገር እንደ ሀገርም ጤናማ ትውልድ ይኖር ዘንድ አጋዥ ተግባር ነው ያሉት የቢሮው ምክትል ኃላፊ፤ በክልሉ ያልተከተቡ ህፃናት እንዳይኖሩ ከማድረግ በተጨማሪ ክትባት ጀምረው ያቋረጡ ህፃናትን በመለየት በተገቢው እንዲከተቡ መደረጉንም አመላክተዋል።
ከተናጠል ይልቅ የተቀናጀ ስራ የተሻለ ውጤት እንዳለው በተግባር የታየበት ስኬታማ የተቀናጀ የጤና ልማት አገልግሎቶችን ማከናወን መቻሉን የጠቆሙት አቶ አሸናፊ፤ በአመቱ ለተመዘገበው ውጤት የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ጨምሮ የዘርፉ አጋዥና አጋር አካላትን እና በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።
በቀጣይ ተግባራዊ መደረግ ያለባቸው ቀሪ ተግባራት ቢኖሩም በአመቱ በተሰራው የተቀናጀ የጤና ስራ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት መቻሉን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ገልፀዋል።
በክልሉ በጤና ኤክስቴንሽንና የማህበረሰብ ጤና መድህን ኘሮግራም የተቀናጀ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
በአጠቃላይ በዋና ዋና የጤና አገልግሎት ዘርፎች የተመዘገበው ውጤት የጋራ ጥረት ስኬት እንደመሆኑ በቀጣይም በጋራ ተቀናጅቶ የመስራቱ ሂደት ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተግባር አፈፃፀም እውቅና የተሰጣቸው አካላትም እውቅናው በዘመቻና በመደበኛ የጤና ተግባራት ላይ የመጣውን ውጤት ለማስቀጠል የሚያስችል አቅምና ተነሳሽነት እንደፈጠረላቸው አስተያየት ሰጥተዋል።
በእውቅና ስነ-ስርዓቱ ከክልሉ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የመጡ የጤና ባለድርሻ አካላትና የዘርፉ አጋዥና አጋር ድርጅቶች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ: አብዱልሃሚድ አወል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የህዝቡን የልማት ፍላጎቶች ለማሟላትና መንግስታዊ አገልግሎቶችን በተገቢው ለመስጠት የውስጥ ገቢ ግብርን አማጦ ለመሰብሰብ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በይፋ ተጀመረ
ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ የልማት ዘርፍ ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ መምጣቱን የዳዉሮ ዞን ግብርና፣ የአካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ ልማት መምሪያ አስታወቀ