ሀዋሳ፡ ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (ደረቴድ) ጂንካን በጋራ እናልማ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ ለ12 ማህበራትና ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን በሥራው ላይ የተሠማሩ ማህበራት ገለጹ፡፡
በግንባታው ዘርፍ ከተሠማሩ ማህበራት መካከል ነጋዬ የግንባታ ማህበር አንዱ ሲሆን፥ የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት እንዳልካቸው አማረና ም/ሰብሳቢ ወጣት ንጋቱ ኃይሌ በጋራ እንደተናገሩት በዚህ የልማት ሥራ ተሳታፊ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡
ሥራው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ በታቀደው መሠረት እንዲተገብሩ የተሰጣቸውን አንድ መቶ ሜትር ቴራዞ የማንጠፍ ሥራ በተወሰነላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
እንደ ነጋዬ ማህበር አስተባባሪዎች ገለፃ በሙያና በጉልበት የሚሠሩ ከ30 በላይ ወጣቶችን በሥራቸው ቀጥረው ተጠቃሚ እያደረጉ ሲሆን ጥሩ የመንግስት ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸው ገልፀዋል፡፡
ህዲ ተይከተ የብሎኬትና ፕሪካስት አምራች ማህበር ቴራዚዮ ከሚያቀርቡ ማህበራት መካከል አንዱ ሲሆን እንዲያቀርብ የተጣለበትን የቴራዚዮ ብዛት አሟልቶ ለማስረከብ ጥረት ማድረግ ላይ መሆኑን የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት አዲሴ ምስለ ገልጿል፡፡
በዚህ ማህበር በተመሳሳይ ከ35 በላይ ሥራ አጥ ወጣቶችን በመቅጠር ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ጠቁመው የመንግስት ድጋፍ የሚበረታታና በዚህ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
ወ/ሮ እየሩሳሌም አልቅማይ በልማቱ የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ሲሆኑ ሁሉም ማህበራት የተሰጣቸውን ሥራ በተሻለ ሁኔታ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልፀው ሥራው በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ እንደ ቴክኒክ ኮሚቴ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እያደረጉ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
የጂንካ ከተማ ከንቲባ አቶ አስፋው ዶሪ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የከተማዋን ወጣቶች ተጠቃሚ ማድረግ ዓላማ ያደረገ ሲሆን በዚህም 12 የሚደርሱ ማህበራትና የተለያዩ ሥራ አጥ ወጣቶች ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ራሔል አብራሃም – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ፈጣንና ቀልጣፋ መረጃን ተጀራሽ በማድረግ የመንግስትና የማህበረሰቡን ተግባቦት ይበልጥ ለማጠናከር የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና የጎላ መሆኑ ተጠቆመ
ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው
በ17 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የሞሪንጋ ጂን ባንክ ለማቋቋም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ