በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽህፈት ቤትም በወማ በርገኖ በላንጎ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።
ወማ በርገኖ በላንጎ ከአባታቸው ከአቶ በላንጎ ባዕሦ እና ከእናታቸው ወ/ሮ እንታሜ ቂዶሬ በቀድሞ ከምባታና ሀዲያ አውራጃ ኦሞ ሸለቆ ወረዳ በአሁኑ ጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጋዕቻ ቀበሌ ሰኔ 24 ቀን 1942 ዓ.ም ተወለዱ።
ወማ በርገኖ በላንጎ ከነሐሴ 01 ቀን 1992 ዓ.ም ጀምሮ የጠምባሮን ባህላዊ አስተዳደር ንግስና (ላሂ ወማ) ማዕረግ ከተረከቡ ወዲህ ቀድሞ የነበራቸውን የህዝብ ኃላፊነት ስሜት ይበልጥ በማሳደግ በማናቸውም ህዝባዊ መድረኮች እርቅንና ፍቅርን፣ አንድነትና መቻቻልን የሚሰብኩ እንዲሁም ከመንግስት አካላት ጎን በመሆን ለአካባቢው ልማት የሚቆረቆሩ አስተዋይ አባት ነበሩ።
በባለፉት ዓመታትም ከቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ተመርጠው የክልሉን ህዝብ በመወከል በሀገራዊ የሀገር ሽማግሌዎች የጋራ ፎረም አባል በመሆን ለሀገር ዘላቂ ሠላም የድርሻቸውን የተወጡ ነበሩ።
ወማ በርገኖ በላንጎ ባለትዳርና የ2 ወንድና የ5 ሴት ልጆች አባት ሲሆኑ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ነሐሴ 05 ቀን 2016 ዓ.ም በተወለዱ በ74 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ወልዴ፤ ወማ በርገኖ በላንጎ ለጠምባሮ ብሔረሰብ ባህልና ታሪክ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አባት ከመሆንም በላይ የብሔረሰቦችን አንድነት የሚያስተሳስሩ ፍቅርና መቻቻልን የሚሰብኩ ታላቅ አባት እንደነበሩ አውስተዋል።
የጽህፈት ቤት ኃላፊው በወማ በርገኖ በለንጎ ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀው ለመላው የጠምባሮ ህዝብ፣ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የምክር ቤቶችን አቅም በማጎልበት የህዝብ ተጠቃሚነትን ማጎልበት ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ ተናገሩ
ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ አላማ በማዋልና ገዢ ትርክትን በማስረጽ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተገለጸ
በምግብ ሰብል ራስን የመቻል አቅም ማሳደግ ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ