የካፋ ዞን ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ማካሔድ ጀመረ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (ደረቴድ) የካፋ ዞን ምክር ቤት 4ተኛ ዙር 11ኛ ዓመት የስራ ዘመን 23ኛ መደበኛ ጉባኤ የዞኑን አስፈጻሚ ተቋማት ሪፖርት በማድመጥ ጀምሯል።

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ የ2016 አመተ ምህረት የአስፈፃሚ ተቋማትን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት በዞኑ የግብርና ስራዎች ላይ አንፃራዊ መሻሻሎች መታየታቸዉን ተናግረዋል።

ለ2015/16 ምርት ዘመን 117ሺህ 384 ሄክታር ማሳ በማልማት ምርታማነትን በሄክታር ከ21 ኩንታል በላይ በማድረስ በጠቅላላ ከ 2 ሚልየን 508 ሺህ 290 ኩንታል ምርት ለመሰሰብ መታቀዱን በሪፖርት አመላክተዋል።

ከዚህም 115 ሺህ 366 ሄክታር ማሳ በማዘጋጀት 114ሺህ 24 ሄክታር በዘር በመሽፈን ከ2 ሚሊየን 556 ሺህ 452 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት ተችላል ብለዋል።

በኢኮኖሚ ዘርፍ በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በኩታ ገጠም እርሻ ዘርፍ የታየው መነቃቃት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በዘርፉ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት 8 ሺህ 846 ሄክታር ማከናወን የተቻለ ሲሆን ከክረምቱ የአዝመራ ወቅት ጋር ሲነጻጸር አፈጻጸሙ 7 ነጥብ 8 በመቶ መሆኑም ተገምግሟል።

በኩታ ገጠም የእርሻ ተግባርም ቀደም ሲል በነበረው አፈጻጸም ላይ 30 ከመቶ በማሻሻል ከ6 ሺህ 92 ሄክታር በላይ ማከናወን መቻሉንም አብራርተዋል።

የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት ረገድም በምርት ዘመኑ የተሻለ እንቅስቃሴ መደረጉን አቶ እንዳሻው ለጉባዔው ባቀረቡት ሪፖርት አስረድተዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በአገዳና ሰብሎች በተለይም በእንሰት ተክል ምርት ላይ የተጀመረው ንቅናቄ አበራታች በመሆኑ  ከባለድርሻ አካል ጋር በመቀናጀት በትኩረት የሚሰራበት ዘርፍ ይሆናልም ብለዋል።

በእንሳትና አሳ ሀብት በአንድ ቀን ዶሮ ጫጩት ርባታን ጨምሮ የህብረተሰቡን ሕይወት በዘላቂነት ሊለውጡ በሚችሉ የግብርና ስራዎች በተለይም የኩታ ገጠምና ሜካናይዝድ እርሻ ተግባራት ላይ ርብርብ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ አቅጣጫ  ተቀምጣል።

ከሀገራዊ የማይክሮ ኢኮኖሚ መሻሻል ጋር ተያይዞ በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮች  ዙርያ መንግስት ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል ሊደርግ እንደሚገባ የጉባኤው አባላት ጠይቀዋል፡፡

መሰረታዊ የሸቀጥ ዕቃዎች የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት፣ የፍጆታ ምርት አቅርቦት እጥረት፣ የህገወጥ ንግድ መበራከትና በአጠቃላይ በንግዱና በትራንስፖርት ዘርፍ የሚታየውን የዋጋ ጭማሪ በዜጎች ኑሮ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ነው የሚያነሱት።

በማህበራዊ ዘርፍ በተለይም የጤና እና የትምህርት ተቋማት በተሟላና ጥራት ባለው ሁኔታ ማገልገል እንዲችሉ በልዩ ትኩረት መፈተሸና መደገፍ እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለተነሱ ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ምላሽና ማብራርያ ተሰጥቶበት የአስፈጻሚ ተቋማት የ2016 በጀት አመት የዕቅድ አፈጻጸም ጸድቋል።

ዘጋቢ፡ በአሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን