በልዩ ወረዳው በ2016 ዓ.ም በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ40 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ልዩ ልዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ገለፀ

ይህ የተገለፀው በልዩ ወረዳው በሌንጫ ቀበሌ የአንድ የአእምሮ ታማሚ ቤተሰብ የቤት እድሳት በተጀመረበት ወቅት ነው።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጁሃር ጀማል በ2016 ዓ.ም በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በልዩ ወረዳው ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እንዲሁም አስተዳደር ጽህፈት ቤት በጋራ በመሆን ከ40 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ልዩ ልዩ ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በልዩ ወረዳው በ14 የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዘርፎች የተለያዩ ተግባራት በወጣቶች ተሳትፎ እየተከናወኑ መሆናቸውን ያስረዱት አቶ ጁሃር በዚህም ከመንግስት ሊወጣ የነበረውን 22 ሚሊየን ብር ለማዳን እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደትም በልዩ ወረዳው 48 አዳዲስ የቤት ግንባታና ነባር ጥገና ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡

የሌንጫ ቀበሌ ስራ አስኪያጅ አቶ አብድኸይ ፈድሉ፤ በ2016 ዓ.ም የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በቀበሌው በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንና ወጣቶችን ጨምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ በጉልበት፣ በገንዘብ እና በቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ተማም ሀጅ አህመድና ወጣት አንዋር ሙስማ የሌንጫ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ ልዩ ወረዳው የተቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመርዳት ዙሪያ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡

የአካባቢው ወጣቶች የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳት ንቁ ትሳትፎ እያደረጉ መሆኑናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ሉባባ ሸምሱ መኖሪያ ቤታቸው በማርጀቱ ልጆቻቸው ለብርድና ለዝናብ ተጋላጭ ከመሆናቸውም ባሻገር የአእምሮ ታማሚ ልጃቸውን ጨምሮ አራት ልጆችን ያለ አባት በማስተዳደር ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

በዚህም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ይደርስባቸው እንደነበር ገልፀው በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ አስፍር ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን