ማዕከሉ ወቅቱ የሚፈልገውን የግብርና ኤክስቴንሽን ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋት የሚያደርገውን ጥረት ይበልጥ በማጠናከር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 05/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የግብርና ምርምር ማዕከሉ ተቋማዊ አደረጃጀቱንና የውስጥ አቅም በማሳደግ ወቅቱ የሚፈልገውን የግብርና ኤክስቴንሽን ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋት የሚያደርገውን ጥረት ይበልጥ በማጠናከር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።

የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል በዙሪያው ለሚገኙ ለአበሽጌ ወረዳ አርሶ አደሮች ከ50 ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍን ቅድመ መስራች የጤፍ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የጤፍ ክላስተር እርሻ ዘር የማስጀመር መርሀ ግብር ተካሄዷል።

በመርሀ ግብሩ ወቅት የምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ቤተል ነክር፤ የወልቂጤ ግብርና ምርምር ከተቋቋመ 30 አመታት መሻገሩን ጠቁመው፣ በዚህ በሰላሳ አመታት ያካበተውን ልምድ በመጠቀም እስከአሁን በቆይታው ያሰራጫቸውን የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው ከብቶችን በአራት አመት ውስጥ ለህብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ አቅም አጎልብቷል ብለዋል።

አክለውም ተቋሙ ምርጥ ዘር ለጉራጌ ዞንና ለአጎራባች ኦሮሚያ ክልል ዞን ከ500 ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍን ምርጥ ዘር በማባዘት ለአርሶ አደሩ እያሰራጨ መሆኑ ገልጸዋል።

በጉራጌ ዞን ከ50 ሄክታር ላይ መሬት የሚሸፍን ምርጥ ዘር በአበሽጌ ወረዳ እንደሚገኝና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል።

የምርጥ ዘር ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ያገኙትን ምርት አቅራቢያቸው ለሚገኙ ምርጥ ዘር አምራች ድርጅቶች በማስረከብና ለሌሎች እንዲዳረስ የማድረግ ዓላማ የያዘ መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

የምርምር ማዕከሉ ተቋማዊ አደረጃጀትና የውስጥ አቅም በማሳደግ ወቅቱ የሚፈልገውን የግብርና ኤክስቴንሽን ተክኖሎጂዎችን ለማስፋት የሚያደርገውን እገዛ ይበልጥ በማጠናከር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ ዶ/ር ቤተል ገልፀዋል።

በቅድመ መስራች የጤፍ ምርጥ ዘር እደላና የዘር ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሱ ጁሀር፤ ማዕከሉ ለአርሶ አደሩ እያደረገው ላለው ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉ የምርምር ማዕከሉ በዙሪያው የሚገኙ አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም ከድጋፍ ጋር ተያይዞ ሲያነሱት የነበረውን ቅሬታ የሚቀርፍ ነው ብለዋል።

አርሶ አደሩ ከባለሙያ ጋር በመተጋገዝ ከምርምር ማዕከሉ በምርምርና ጥናት የሚወጡ አዳዲስ የግብርና እና የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በማስፋት ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ዋና አስተዳዳሪው ገልፀዋል።

የአበሽጌ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ ተወካይ አቶ ሙላቱ ደሳለኝ በወረዳው ከ29 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የመኸር ሰብሎች እየለማ መሆኑ ገልፀው እንደሀገር አርሶአደሩን እየፈተነ ያለውን የምርጥ ዘር ፍላጎት የማሟላት ችግር ለመቅረፍ ከወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ለአበሽጌ ወረዳ የወልቂጤ ግብርና ምርምር ማዕከል በከብት እርባታ፣ በሰብል ብዜት እና በምርጥ ዘር አቅርቦት በማገዝ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ወደ አርሶ አደሮች እያሸጋገረ ይገኛል ያሉት ሀላፊው ተወካይ፤ በወረዳው በሶስት ቀበሌ የሚሠራው የጤፍ ቅድመ መስራች ዘር የማባዛት ስራ ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

በወረዳው አምበልታ፣ ማመዴ እና ጣጤሳ ቀበሌያት አግኝተን ያነጋገርናቸው አርሶአደሮች መካከል አርሶ አደር ኑረዲን አብድርሽ፣ ዳዊት አሰፋና አበበ ገብሬ በሰጡት አስተያየት በተደረገላቸው ምርጥ ዘር ድጋፍ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡ ተግባሩን ለማሳካት ኩታ ገጠም እርሻ ቴክኖሎጂ በማላመድ በግብርና እና በእርባታው ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ አማረ መንገሻ – ከወልቂጤ ጣቢያችን