የሀላባ ዞን ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ማስፈጸሚያ ከ1 ቢሊዮን 6 መቶ 68 ሚሊዮን 9 መቶ 01 ሺህ ብር በላይ አጸደቀ

ምክር ቤቱ 4ኛ ዙር 9ኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት እያካሄደ ነው።

ምክር ቤቱ ባለፈው ሣምንት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የምክር ቤት አባል ለአቶ ከድር መሐመድ የህሊና ጸሎት በማድረግ ነው ጉባኤውን የጀመረው።

የሀላባ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ መሀመድ አሚን ሀጂ ማህዲ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ ምክር ቤቶች በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና በመንግሥት አሠራር የህዝብ ተሳትፎን በማረጋገጥ በህብረተሰቡ ኑሮ፣ መብትና ነፃነት ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንዲታይና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የሚያደርጉ ዋነኛ ተቋማት ናቸው ብለዋል።

በሀገራችን በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ትኩረት ተደርገው የመጡ ውጤቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ያሉት ዋና አፈ ጉባኤው፤ የግብርናው ዘርፍ በሀገርቷ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ፈይዳው ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎችም ዘርፎች በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንም አስረድተዋል።

በዞኑ ሰላምና ፀጥታ በሌሎችም ዘርፎች የመጡ ለውጦችን አጠናክሮ ማስቀጠል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም አቶ መሀመድ አሚን ተናግረዋል።

በዞኑ በተለያዩ ዘርፎች በተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉ የሚበረታታ ቢሆንም ከህብረተሰቡ ፍላጎትና ካለው ዞናዊ አቅም አንፃር በቀጣይ ብዙ ስራ መስራትን የሚጠይቅ ተግባር ነው ብለዋል።

ምክር ቤቱ ባደረገው የክትትልና የመስክ ምልከታ ጉብኝት የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎችን በመደማመጥ ያሉትን ችግሮች ከመፍታት ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ማረም እንደሚገባም አመላክተዋል።

የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን ሁሴን የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2017 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኢኮኖሚው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በከተማና በገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ ስራዎች፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት የተቀመጡ ግቦች ላይ የተመዘገቡ ለውጦችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በቀረበው አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ተሰጥቷል።

ምክር ቤቱ ለ2017 በጀት ዓመት ማስፈጸሚያ 1 ቢሊዮን 6 መቶ 68 ሚሊዮን 9 መቶ 1 ሺህ 8 መቶ 16 ብር ረቂቅ በጀት ለምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

በጉባኤው የሀላባ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትና 2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎ በምክር ቤቱ የፀደቀ ሲሆን የተለያዩ ሹመቶችንም ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

ዘጋቢ: አብዱልሰመድ አወል – ከሆሳዕና ጣቢያችን