የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማፋጠን ከአበዳሪ ተቋማት ጋር እየተሰራ ነው

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 03/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርሶአደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማፋጠን ከአበዳሪ ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የገጠር መሬት አስተዳደር አጠቃቀም ኤጀንሲ ገለጸ።

የአርሶአደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት ለመሥራት ያለመ መድረክ ተካሂዷል።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የገጠር መሬት አስተዳደር አጠቃቀም ኤጀንሲ ብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ አያያዝ ስርአትን በማስፈን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማፋጠን ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በመስራቱ ተጨባጭ ውጤት በመመዝገብ ላይ ይገኛል።

በክልሉ የብድር አገልግሎት ያልጀመሩ 12 የወረዳ መዋቅሮች መኖራቸውን በካልም ፕሮጀክት የብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ስርአት አስተባባሪ አቶ ሄኖክ ዮሴፍ ይህንን ክፍተት ለመሙላት በቀጣይ ይሰራል ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ ሴት አርሶ አደሮች በገጠር መሬት አስተዳደር አሰራር ውስጥ ገብተው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች ድርሻ ዘጠኝ በመቶ በመሆኑ ቀጣይ ሰፊ ስራ ይጠይቃል ብለዋል።

የገጠር መሬት አስተዳደር አጠቃቀምን በማዘመን ከፋይናንስ ተቋማት ጋር መስራት በመቻላቸው የአከባቢያቸውን አርሶአደሮች ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ከወላይታ እና ጎፋ ዞን የተገኙ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

በመድረኩ የተገኙት የመተማመን ማይክሮ ፋይናንስ አበዳሪ ተቋም ተወካይ አቶ በለጠ ባቢሶ እንደገለጹት የመሬት ይዞታ ሰርተፍኬትን በመያዝ በግልም ሆነ በቡድን የብድር አገልግሎት ፈልገው ለመጡ ደንበኞች ከ3 ሚሊየን ብር በላይ ብድር መስጠታቸውን ጠቅሰዋል።

የደቡብ ለኢትዮጰያ ክልል መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ኤጀንሲ ስራ-አስኪያጅ አቶ ኖህ ታደለ እንደገለጹት 2ተኛ ዙር የመሬት ልኬት በተጠናቀቀባቸው አከባቢዎች የሚገኙ ባለይዞታዎች ሰርተፍኬታቸውን በማስያዝ ከአበዳሪ ተቋም ብድር እንዲያገኙ ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል።

እንደ ክልል የመሬት ባለቤትነት ሰርተፍኬትን በማስያዝ አርሶአደሩ ከአበዳሪ ተቋም አገልግሎት ማግኘት መጀመሩ በስኬት የሚጠቀስ ነው ብለዋል አቶ ኖህ።

የአበዳሪ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናና ወጥ አሰራር ከመከተል ረገድ የሚስተዋሉ ማነቆዎች ሊፈቱ እንደሚገባ ጠቅሰው የሴት አርሶአደሮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል በቀጣይ በቅንጅት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ አሰግድ ተረፈ- ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን