በክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ አረጋዊያን ደስታቸዉን ገለፁ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 03/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2016 የክረምት ወራት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የ22 ቤቶች አዲስ ግንባታና እድሳት እየተደረገ መሆኑን የጂንካ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት አስታዉቋል፡፡

ወ/ሮ ወጋዬሁ ጅፋርና አቶ ቡቁሚ ደይስሚ በጋራ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም ይኖሩበት የነበረዉ የመኖሪያ ቤታቸዉ በክረምት ወቅት ቤታቸው ዝናብ እንደሚያፈስ ተናግረው አሁን ግን በጎ ፍቃደኞችና መንግስት እየሰሩላቸዉ ባለዉ የቆርቆሮ ቤት መደሰታቸዉን ተናግረዋል፡፡

ከበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች መካከል በጎነት ለራስ ነው ያሉት በኢንተርፕራይዝ ማህበር የተደራጁ የሀዲ ተይከቴ የጥረት ብሎኬትና አምራች ማህበር ሰብሳቢ አቶ አዲሴ ምስሌ እና አቶ ኪያ ምስሌ በጋራ እንደገለፁት በጎ ስራ መስራት የህሊና እርካታን ከመስጠቱ ባሻገር በፈጣሪ ዘንድም የሚያስመሰግን በመሆኑ ሁለት ወንድማማቾች ከኢንተርፕራይዝ ጽ/ቤት ጋር በመነጋገር በዘንድሮዉ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለወ/ሮ ወጋየሁ ጅፋርና አቶ ቡቁሚ ደይስሚ 33 ቅጠል ቶርቆሮ የመኖርያ ቤት በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡

የጂንካ ከተማ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካኒ አንዳ፤ የስራ እድል የተፈጠረላቸዉ ወጣቶች በበጎ ተግባር ተሳትፈዉ ምድራዊ እርካታና ሰማያዊ ዋጋ እንዲያገኙ   በአምራችና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተደራጁ ማህበራትን በማስተባበር በአረጋዊያን ቤት እደሳትና ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

የጂንካ ከተማ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ያለም ግርማ በበኩላቸዉ ለአረጋዊያንና አቅም ደካሞች የሚደረግ ድጋፍና እገዛ በበጋም ሆነ በክረምት ወራት ቀጣይነት ያለዉ በመሆኑ በዘንድሮዉ የክረምት ወራት በጎ ፍቃድ አገልግሎት 22 ቤቶች አዳዲስ ግንባታና እድሳት የሚፈልጉ ቤቶችን በመለየት አሁን ላይ 3 አዳዲስ ቤቶችና 1 የጥገና ስራ እየተሰራ ሲሆን ቀሪ ቤቶችን ለመስራት የሀብት ማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የጂንካ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ዘሪሁን በዘንድሮዉ የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ተግባር አገልግሎት ከተለዩ የስምሪት መስኮች መካከል ድጋፍ ለሚሹ  አቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ ሀብት በማሰባሰብ  የአዲስ ቤት ግንባታዎችና የእድሳት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን