ሀዋሳ፡ ነሐሴ 03/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን የሸኮ ከተማ አስተዳደር ምስረታ ተካሂዷል፡፡
የሸኮ ከተማ አስተዳደርን በይፋ ያስጀመሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ግርማ ባሻ ለከተማው መመስረት ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በሁሉም መስኮች የተጣለበትን ኃላፊነት ይወጣ ዘንድ ተገቢውን ድጋፍ በማደረግ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን ከተማው ከፍተኛ ሀብት ያለበት በመሆኑ ይህን ሊሸከም የሚችል ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና እድገት እንዲያስመዘግብ ሁሉም ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ተወካይ አቶ ፀጋዬ ሀይሌ በበኩላቸው በትኩረት ከተሰራ ከተማው የንግድና ኢንዱስትሪ ማዕከል ማድረግ እንደሚቻል ገልጸው ለዚህም ቢሮው ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ታምራት ምናሴ በበኩላቸው የከተማውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
በቤንች ሸኮ ዞን 6 ወረዳዎችና 2 ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ሲሆን ዛሬ የተመሰረተው የሸኮ ከተማ አስተዳደር በዞኑ ሶስተኛው ሆኗል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ምሰረታ የምክር ቤት የጉባኤ አባላትን ያጸደቀ ሲሆን የከንቲባ አቶ ታምራት ምናሴን እንዲሁም የአስፈፃሚ አካላትን ሹመት ሰጥቷል።
ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ