የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት ማስፈጸሚያ ከ5 ቢሊየን 294 ሚሊዮን ብር በላይ አፀደቀ

ምክር ቤቱ 4ኛ ዙር 11ኛ አመት 26ኛ መደበኛ ጉባኤው በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በሰሞኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የህሊና ጸሎት በማድረግ ነው ጉባኤውን የጀመረው።

የጉራጌ ዞን ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ልክነሽ ሰርገማ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በሀገራችን በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች የመጡ ለውጦችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች ሉአላዊነታቸውን ጠብቀው በህገ መንግስት የተሰጣቸው ዋና ዋና ተግባራትም ውክልና ማረጋገጥ፣ ህግ ማውጣትና የክትትልና ቁጥጥር ስራ መፈጸም እንደሆነ በማንሳት፤ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት የዞኑ ምክር ቤት የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ጠንካራ ክትትል እና ልዩ ድጋፍ በመደረጉ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

የኢኮኖሚያችን ዋነኛ ማገር የሆነውን የግብርና ዘርፍ በሃገሪቱ እንዲሁም በዞኑ ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም በዚህም በዘርፉ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አፈ ጉባኤዋ አስታውቀዋል።

በተለይም ከሰላምና ጸጥታ አንጻር የመጡ ጅምር ለውጦችን አጠናክሮ ማስቀጠል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ጠቁመዋል።

መንግስት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች በባለሃብቱና በህብረተሰብ ተሳትፎ 277 ሚሊየን ብር በማሰባሰብ ለመንገድ ልማት ዘርፍ መዋሉን ተናግረዋል።

የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የተጀመሩ የሰንበት ገበያዎች ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በሌሎችም ቀናት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ወይዘሮ ልክነሽ አሳስበዋል።

በዞኑ በተለያዩ ዘርፎች በተሰሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉ የሚበረታታ ቢሆንም ከህብረተሰቡ ፍላጎትና ካለው ዞናዊ አቅም አንጻር በቀጣይ ብዙ ስራ መስራትን ይጠይቃል ሲሉ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ባደረገው የክትትልና ምልከታ ስራዎች የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎችን ከማድመጥና ከመፍታት አንጻር ያሉ ጉድለቶችን በቀጣይ መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው የ2016 በጀት አመት ዞኑ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ቢያልፍም አብዛኞቹ ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ ተናግረዋል።

በሁለቱም ዞኖች የሚገኙ ወንድማማች ህዝቦችና የአመራሮችን አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር ስራዎች የተሰሩ ሲሆን በተለይም የማህበረሰቡን ባህልና ቋንቋን ለማሳደግ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የ2016 በጀት አመት አፈጻጸም ሪፖርት በጉራጌ ዞን ፕላንና ልማት መምሪያ ሃላፊ በአቶ ከበደ ሃይሌ ቀርቧል።

በዚህም በዞኑ በተጠናቀቀው የ2016 በጀት አመት በኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በከተማና በገጠር ስራ እድል ፈጠራ ስራዎችን የማጎልበት፣ የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነትን የማሻሻል በተለይም በማህበራዊ ልማት ዘርፍ በትምህርት፣ በጤና፣ በቱሪዝም እና በሌሎችም ዘርፎች ላይ የተቀመጡ ግቦችን ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አቶ ከበደ ተናግረዋል።

በቀረበው ሪፖርት የምክር ቤት አባላት ውይይት የተደረገበት ሲሆን ከሰላምና ጸጥታ አንጻር ያሉ ውስንነቶች፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽነት፣ በፋይናንስ ግልፀኝነትና ተጠያቂነት፣ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ፍትሃዊነት፣ በመሬት አቅርቦት፣ የወልቂጤ ሆስፒታል እና በዞኑ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ያለመጠናቀቅ ችግር መኖር ከተነሱ ሃሳቦች መካከል ይገኙበታል፡፡

ከምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎችም በጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በአቶ ላጫ ጋሩማ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት ስራ ማስፈጸሚያ 5 ቢሊየን 294 ሚሊዮን 938 ሺህ 618 ብር እንዲሆን ረቂቅ ለምክር ቤት አባላት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡

ዘጋቢ፡ አስቻለው አማረ – ከወልቂጤ ጣቢያችን