የዛሬው እንግዳችን አንዱዓለም መንግስቱ ናቸው፡፡ የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ስራ አስኪያጁን የህይወት ተሞክሮአቸውንና እንዲሁም በተቋም ስኬታቸው ዙሪያ ላነሳንላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ መልካም ንባብ!
በጌቱ ሻንቆ
ንጋት፡- ለቃለ መጠይቃችን መመቸት ብቻ ሳይሆን ወጣት እንደመሆንህም መጠን አንተ ልበል ወይስ አንቱ?
አቶ አንዱዓም መንግስቱ ፡- አንተ ብትለኝ ደስ ይለኛል፡፡
ንጋት ፡- አንዱዓለም እስኪ ራስህን አስተዋውቀን?
አቶ አንዱዓም ፡- አንዱዓለም መንግስቱ እባላለሁ፡፡ የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ነኝ፡፡ የተወለድኩት አርባ ምንጭ ከተማ ነው፡፡ እናትና አባቴ አርባ ምንጭ አካባቢ ለረጅም ጊዜ በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ እዛው ባገለገሉበገት አካባቢ በ1978 ዓ,ም ነው የተወለድኩት፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በኮንሶ ዞን ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴንም እዛው አርባ ምንጭ ከተማ ነው የተከታተልኩት፡፡
ንጋት፡- በምን ዓይነት የትምህርት መስክ ነው የጨረስከው? ትምህርትህስ ላይ እንዴት ነህ?
አንዱአለም፦ ሁለተኛ ዲግሪዬን የተማርኩት አዲስ አበባ የንቨርሲቲ ነው። ካለፍኩና ትምህርት ከጀመርኩ በኋላም ጥሩ የትምህርት ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ የማስተርስ ዲግሪዬን የጨረስኩት 3.99 ውጤት በማስመዝገብ ነው፡፡ የመመረቂያ ፅሁፌም በጣም ጥሩ ነው የተባለው፡፡ አንድ ኤክሰለንት ሶስት በጣም ጥሩ የነበረ ሲሆን ከሶቱ በጣም ጥሩዎች አንዱ የኔ ነበር፡፡ ሁለተኛ ዲግሪዬን የያዝኩት በክሊኒካል ኤንድ ካውንስሊንግ ማኔጅመንት ነው።
ከዚህ በኋላም የማስተማር ፍላጎት ነበር ውስጤ ያለው፡፡ ደብረ ብርሀን ዩንቨርሲቲ አመልክቼ ነበር፡፡ የመምህራን ልጅም ስለሆንኩ የማስተማር ፍላጎቴ ከፍተኛ ነበር፡፡ ደብረ ብርሀን ዩንቨርሲቲ ለፈተና ቀርቤ አለፍኩ፡፡ ይሁንና ለጉረጌ ዞን ጤና መምሪያ ውል ፈርሜ ነበር፡፡
ንጋት፡- ደብረ ብርሀን ዩንቨርሲቲ ሄድክ ወይስ ጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ተመለስክ?
አንዱዓለም ፡- ወደ ጉራጌ ዞን ተመልሼ ለአምስት ወራት ያህል አገለገልኩ፡፡ ለአምስት ወራት አካባቢ ካገለገልኩ በኋላ የቡታጅራ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ሆኜ እንዳገለግል ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ በሰዓቱ እንቢታዬን ነው ያሳየሁት፡፡ የመሪነት ልምድም ስለሌለኝ ጥያቄው ፈታኝ መስሎ ነው የታየኝ፡፡ ሆኖም አባቴ ጠንካራ ሰው ነው፡፡ በጊዜው ሀላፊነቱን እንድቀበል መከረኝ፡፡ አባቴ ህብረተሰቡን ማገልገል አለብህ የሚል ጫናም ፈጠረብኝ፡፡ በዚህ ምክንያት 2005 ዓ.ም ላይ ወደ ቡታጅራ ሆስፒታል መጣሁ፡፡
ንጋት፡- ቡታጅራ ዞናል ሆስፒታል ከገባሀ በኋላስ? የመማር ፍላጎትህን ገታኸው?
አንዱዓለም ፡- አልተገታም ፡፡ ከስራዬ ጎን ለጎን የ ‘‘ ኦን ላየን ’’ ስልጠናዎችን በመውሰድ እራሴን ለማጎልበት ጥረቶች አድርጌያለሁ፡፡
ንጋት፡- ከወሰድካቸው ስልጠናዎች መካከል የተወሰኑትን ጠቀስ ጠቀስ አድርግልን ፡፡
አንዱዓለም ፡- ከ አይ . ኤች . አይ ፒ. ተቋም የአመራርነት የአጭር ጊዜ ስልጠና ወስጃለሁ፡፡ እንደዚሁ ‘‘ ሊደርሺፕ ኤንድ ገቨርናንስ ’’ በሚል ርዕስ ሀገር ቤት ከሚገኝ ተቋም የረጅም ቀናት ስልጠና ወስጃለሁ፡፡ በህክምና ጥራት አስተዳዳር ዓለም አቀፍ ስልጠና ወስጃለሁ፡፡ እንደዚሁም “ኮቺንግ ሜይንቴር ’’ ላይ ሀገር ቤት ውስጥ ዕውቅና ካለው ተቋም አጭር ኮርስ ወስጃለሁ፡፡
ንጋት ፡- ቀጠልክ እንዴ?
አንዱዓለም ፦ ሁለተኛ ዲግሪዬን በጨረስኩ በአራት ወራት ልዩነት ነው የፒ.ዔች.ዲ ትምህርቴን የቀጠልኩት፡፡
ንጋት ፦ ወደ ቡታጅራ ሆስፒታል ስትመጣ በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን እንድትደፍን ተፈልጎ የመጣህ ይመስለኛል። ስትመጣ ምን ክፍተቶች ነበሩ?
አንዱዓለም ፦ ከኔ የቀደሙት ስራ አስኪያጆች ሆስፒታሉ ውስጥ የየራሳቸውን አሻራዎች አስቀምጠዋል። ቢሆንም ክፍተቶች ነበሩ። የመጀመሪያው ክፍተት የሠው ሀይሉ ነው።
ሁለተኛው የመሰረተ ልማት ክፍተት ነው ሶስተኛው የህክምና መሳሪያዎች እጥረት እና ውስን አገልግሎቶች ነበር የሚሰጠው ፡፡ ሆስፒታሉ ለመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እንደተገነባ ነበር፡፡ አገልግሎቶቹ እንዲጨምሩ ግን ይፈለጋሉ፡፡ ነገር ግን ለዚያ የሚሆኑ መሰረተ ልማቶች ደግሞ የሉም፡፡ መሰረተ ልማቶች ከሌሉ ሜዳ ላይ ህክምና መስጠት አትችልም፡፡ ሶስተኛው የህክምና መሳሪያዎች ናቸው፡፡ በቂ የህክምና መሳሪያዎች አልነበሩም ፡፡ እኔ ስመጣ የራጅ ማንሻ ጭምር አልነበረም ፡፡ ማሽኑ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት በመስጠቱ ተበላሽቶ ነበር፡፡ በዚህም ለራጅ አገልግሎት ፍለጋ ህብረተሰቡ አዲስ አበባ ይሄድ ነበር፡፡
ንጋት፡- ይሄኮ በሽተኛ ከመላክ የተለየ አይደለም፡፡
አንዱዓለም ፡- አዎ። የተለየ አይደለም፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የህክምና መሳሪያዎች በበቂ መጠን አልነበሩም፡፡ ይህም በአገልግሎት አሰጣጣችን ላይ እንቅፋት ነበር፡፡ አራተኛው የህክምና አገልግሎት አሰጣጣችን ጥራቱን የተጠበቀ አልነበረም፡፡ ባጠቃላይ እነዚህ ነገሮች በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የተደቀኑ ፈተናዎች ነበሩ፡፡
ንጋት፡- ግማሽ ወይም ከዚያ በላይ የህክምና አገልገሎት የሚሰጠው በህክምና መሳሪያዎች ላይ ተመርኩዞ ይመስለኛል፡፡
አንዱዓለም ፡- አዎ። እንደዚያ ነው፡፡ የአገልግሎት አሰጣጣችን አቅም በህክምና መሳሪያዎች ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ የጠቀስኳቸውን አራት መሰረታዊ ጉዳዮች እንዴት ነው መፍታት የምንችለው የሚል ጥያቄ በማንሳት ከቦርዱ ጋር፣ ከተቋሙ ማኔጅነመንት ጋር መከርን፡፡ በጋራ ሆነን ዕቅድ ወደማዘጋጀት ተግባር ነው የተሸጋገርነው፡፡ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የፋይናንስ አቅም ያስፈልጋል፡፡ ያለን የፋይናንስ አቅም ደግሞ ውሱን ነው፡፡ የሚመደብልን በጀት ከደሞዝና ከሰራተኛ ጥቅማጥቅም ያለፈ አይደለም፡፡ ምንም ዓይነት የካፒታል በጀት የለንም፡፡
ንጋት፡- ምናልባት ለችግሩ ምክንያት የሆኑ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ነበሩ?
አንዱዓለም ፡- በርግጥ እንደዞንም የበጀት ዕጥረቶች ነበሩ፡፡
ንጋት፡- ግንኮ የበጀት ዕጠረቶች ቢኖሩም፤ ለምሳሌ ያህል የፖለቲካ አመራሩ ይህን ችግር ለመሻገር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በመጋበዝ ችግሩን የመሻገሪያ መንገድ የማበጀት ዕድል ያለ ይመስለኛል፡፡ ለዛ ነው መጠየቄ፡፡
አንዱዓለም ፡-ማህበረሰቡ በተደጋጋሚ መንግስት የሚመድብልን በጀት አነስተኛ ነው የሚ ጥያቄ ያነሳ ነበር፡፡ በርግጥ አሁንም አዲስ ዞን እንደመሆኑ እጥረቶች አሉ፡፡ ለመድሀኒት ተብሎ እንኳን ከመንግስት የሚመደብልን በጀት አልነበረም፡፡ ለካፓታል ተብሎ የሚመደብልን በጀት አልነበረም፡፡ አሰታውሳለሁ፡፡ የዛሬ አራት ዓመት የከፋ ፈተና ላይ ስንወድቅ አንድ የካፒታል ገንዘብ ተመድቦልን ነበር ፡፡ ሶስት ሚሊዮን ብር በዚህም ጀነሬተር ግዥ ፈፀምን፡፡
ባጠቃላይ የጠቀስኳቸውን መሰረታዊ ጉድለቶች ያለ ገንዘብ አቅም ማሟላት አይቻልም፡፡ በዚህ ምክንያት ከማኔጅመንቱ ጋር በመምከር ሶስት ዓይነት አማራጮችን አስቀመጥን፡፡
አንደኛው አማራጭ ሀገር ውስጥ ያሉ መንግስታዊ ያልሁኑ ድርጀቶችን መድረስ ነበር፡፡ ሁለተኛው የፋይናንስ ምንጭ ሊሆነን ይችላል ብለን ያሰብናቸው ከሀገር ውጪ ያሉ በተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎች ላይ የሚሳተፉ ድርጅቶችን ነበር፡፡ ሶስተኛው ደግሞ የውስጥ አቅማችን ምን ይመስላል የሚለው ጉዳይ ነበር፡፡ ይህንንም ጥያቄ አንስተናል፡፡ የምንሰበስባቸውን ገቢዎች ለችግሮቻችን መፍቻ አቅም አድርገን ለመጠቀም ተነሳን፡፡
እነዚህን መነሻዎች ይዘን የአምስት ዓመት ስትራተጂክ ፕላን አዘጋጀን፡፡ በዚህ ስትራተጂክ ፕላናችን ላይ የት መድረስ እንዳለብንም ለይተን አስቀመጥን፡፡ ግባችን ሆስፒታሉን በአምስት ዓመታት ውስጥ ወደ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ማሳደግ የሚል ነበር፡፡ በስራተጂክ ፕላኑ መሰረት ማን ምን ይቻል? ህብረተሰቡ ምን ይቻል? ሆስፒሉ በውስጥ ገቢው ምን ይቻል? አጋሮቻችን ምን ይቻሉ? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተን በማቀድ ከለየን በኋላ ሁለት ነገሮች ጎን ለጎን እንዲሄዱ ነው ያደረግነው፡፡
እኔ ወደዚህ ተቋም በመጣሁ ጊዜ ፣ በ2005 ዓ.ም ማለት ነው፣ 225 ሰራተኞች ሆስፒታሉ ነበሩት፡፡ በዚህም የሆስፒታሉ የሰው ሀብት አቅም ላይ መስራት አለብን ብለን ተነሳን፡፡ የወሰድነው አማራጭ ሆሲፐታሉ ያለውን የሰው ሀይል ማስተማር ነበር፡፡ በዚህም ሆስፒታላችን ውስጥ ያሉ ሀኪሞችን ወደ ስፔሻሊቲ ማስተማር ፡፡ ማሳደግ አለብን ብለን መንገድ ጀመርን፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውን ደግሞ ወደ ሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ አስፋጊነት ላይ አተኮርን፡፡ በዚያው መጠን ዲፕሎማ ያላቸውን ወደ ዲግሪ ምሩቅነት ማሸጋግር እንዲሁም በሁሉም ዘርፍ ቅጥር መፈፀም አለብን ብለን ተነሳን፡፡ መጀመሪያ በሰው ሀብቱ አቅም ላይ መሻሻሎች ካሳየን ሌሎች ነገሮች ተከትለው ይመጣሉ የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስን፡፡ በዚህ ላይ ሰራን፡፡ ሶስት ብቻ የነበሩት የስፔሻሊቲ ሀኪሞች አሁን 18 ደርሰዋል፡፡
ንጋት፡- እንሻገር ወደ መሰረተ ልማት የሆስፒታሉ ፈተናዎች?
አንዱዓለም ፡-ቅድም እንደገለፅኩልህ የመሰረተ ልማቱ አለመሟላት ትልቅ ፈተና ነበር፡፡ ከመንግስት ለካፒታል ተብሎ የሚመደብ አንዲትም ብር የለችንም፡፡ ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር ፕሮጀክቶችን መቅረፅ ነው፡፡ የቀረፅናቸው ፕሮጀክቶች ለተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አደረስን፡፡ ይህም አንዱ ስራችን ሆነ፡፡ የስትራተጂክ ዕቅዳችን አንዱ አካል ነበር፡፡ በስትራተጂክ እቅዳችን ላይ ሆስፒታላችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን አለበት ብለንም ተነስተን ነበር፡፡ በዚህ መልኩ በሽልማት ያገኘናቸውን የገንዘብ አቅሞች ጥቅም ላይ አውለናል፡፡ በዚህም ወደ 15 ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ አድርገናል፡፡ ያገኘናቸውን ሽልማቶች ለፌሽታና ለሰራተኞች ማከፋፈል ተግባር አልተጠቀምንበትም፡፡
በሌላ በኩል በመሰረተ ልማት ረገድ የገጠመንን ፈተና ለመሻገር ከሀገር ውጪ ያሉ አቅሞችን መጠቀም አለብን የሚል ትልም አስቀምጠን ነበር፡፡ የዚሁ አካባቢ ተወላጅና ሀገር ወዳድ የሆነችውን ፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሀን ማግኘት እንዳለብን ወሰንን፡፡ ነገር ግን በቀላሉ የምትገኝ አልሆነችም፡፡ ፕሮፌሰሯ በስራ የተወጠረች ናት፡፡
ንጋት፡- ፕሮፌሰር ስናይት ብብዙ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር የምትፈለግ ናት፡፡
አንዱዓለም ፡- አዎ ፡፡ ከማኔጅመንት አባላቱ መካከል ሁለታችን በኢሜይል አድራሻዋ መልዕክት ላክንላት፡፡ ባጋጣሚ ደግሞ ወንድሟም ከአሜሪካን ሀገር መጥቶ እዚሁ ቡታጅራ ነበር፡፡ እኔና የቦርዱ አባል የሆኑት አቶ በቀለ አየለ እና አቶ ፍቃድ አሶሬ በጋር ወንድሟን አቶ ዳኛቸውን በማወያየት ለወንድሟ ስትራተጂክ ዕቅዳችንን ለፕሮፌሰር ሰናይት እንዲያደርስልን በእጅ ሰጠን፡፡ ይህን ባደረግን ከተወሰኑ ጊዜያትበኋላ ምላሽ አገኘን፡፡ ደስተኛ መሆኗን ገለፀችልን፡፡ ሆስፒታሉን ለመጎብኘትም እቅድ በመያዝ በርካታ አካላትን በመያዝ ሆስፒታሉን ጉብኝት አደረገች ሆስፒሉም በመሰረታዊነት ያለበትን ጉደለት ማሳየት ተቻለ ሆስፒታሉም ለእንግዶቹ ባህላዊ አቀባባል አደርገላቸው፡፡
ፕሮፌሰሯ ባየቻቸው ነገሮች ልቧ ተነካ፡፡ ወዲያውኑ በአጭር ጊዜ የሚያልቁ ሁለት ፕረጀክቶች ተግባራዊ እንደምታደርግ አስታወቀችን፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የእናቶችና ህፃናት እንዲሁም የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ፣ ሙሉ የህክምና መሳሪያዊች የተሟሉለት ህንፃ እንዲገነባ ተደረገ፡፡ ህንፃው 2632 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነው፡፡ ሁለት ኮንቴይነር የህክምና መሳሪያዎችም ገብተዋል፡፡ መሳሪዎቹ በመገጠም ላይ ናቸው፡፡
ንጋት፡- ከምትሰጧቸው የስፔሻሊቲ አገልግሎቶች የተወሰኑትን እናንሳ?
አንዱዓለም ፡- አሁን ቡታጅራ ሆስፒታል ከሚታወቅባቸው የስፔሻሊቲ አገልግሎት አንዱ መድሀኒት የተላመደ የሳንባ በሽታ ህከምና ነው፡፡ ህክምናው ስልጤ ዞን ያሉ ጤና ጣቢያዎች በጉራ ዞን ፣ ለምስራቅ ጉራጌ ዞን፣ ለጉራጌ ዞን፣ ለስልጤ ዞን፣ ለየም ዞን እንዲሁም በአጎራባች ኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የሚልኳቸው በሽተኞች መጥተውና ታክመው የሚድኑበት ፣ እኛም በሀገር አቀፍ ደረጃ የምንታወቅበት አገልግሎታችን ነው፡፡ ለላው በሆስፒታሉ በአሁኑ ሰአት ከአስራ በላይ ስፔሻሊስት አገልግሎቶች ይሰጣል ።
ንጋት ፦ በመጨረሻ የምታመሠግነው ሠው ካለ ዕድል ልሰጥህ?
አንዱዓለም፦ ባለቤቴን።
More Stories
“ሳንቲም ሲጥሉልኝ አመስግኜ ነው የምመልሰው” – ወጣት ማህቶት በለጠ
“ጥበብ ነገሮችን በተለየ መንገድ ማየት መቻል ነው” – ተወዛዋዥ ተስፋ ጽዮን ንጉሴ
ትኩረት ሊሰጠው ይገባል!