“አንድ ቦታ ላይ ታጥሬ መቅረትን አልፈልግም” – ወጣት አይናዲስ ታረቀኝ
በገነት ደጉ
በዛሬው እትም ለየት ያለች ባለታሪክ ይዘን ቀርበናል፡፡ ባለታሪካችን ታሪክ ጠቃሚ እና ልምድ እንደምትወስዱም እርግጠኛ ነንና ተከታተሉን፡፡ ባለታሪካችን የአውራ አምባ ማህበረሰብ አባል ናት፡፡ ወጣት አይናዲስ ታረቀኝ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በአውራ አምባ ማህበረሰብ ውስጥ ነው፡፡ ወላጆቿ የአውራ አምባ ማህበረሰብ አባል ናቸው፡፡ “ልዩ ስሙ ጡረኝ ተብሎ በሚጠራ ጎጥ ተወልጄ ያደኩ ሲሆን የሚታወቀው ግን የአውራ አምባ ማህበረሰብ በመባል ነው፡፡
የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩት እዛው አውራ አምባ ማህበረሰብ ውስጥ ነው፡፡ አካባቢው ላይ ኮሌጅ እና ዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንጂ የሌለው ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ትምህርት ቤት እንዳለ ትናገራለች፡፡ 2002 ዓ.ም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በአውራ አምባ ሲከፈት ዕድሉን በማግኘት ወደ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ በወቅቱም ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ በተከፈተው አዲስ ራዕይ ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ተከታትዬ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴንም እዛው አዲስ ራዕይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመማር የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን አጠናቀቅኩ፡፡
በትምህርት ቤት በነበረኝ ቆይታ ልዩ ተስጥኦ ስላለኝ በግጥም እና በስነ-ጽሑፍ ላይ ትንሽ ትንሽ እሞክር ነበር፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ ከልጅነቴ ጀምሮ የምወደው ሙያ በመሆኑ ገና በጠዋቱ ህልሙ ስለነበረኝ እና መጽሐፍ ማንበብም ላይ አተኩር ነበር፡፡ መድረኮችን ባገኘሁ አጋጣሚ የስነ-ጽሑፍ ሥራዎቼን አቀርባለሁ፡፡ መድረኮችን የመምራት እድልም ነበረኝ፡፡ በሬድዮ 180 የሚባል ፕሮግራም ላይ ቅዳሜ መዝናኛ ግጥም በማንበብ ላይ እሳተፍ ነበር፡፡ የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ የመምጣት እድሉ ስለነበረኝ ጦቢያ ላይ ዋናው መድረክ ሳይሆን እስቱዲዮ ላይ እሳተፍ ጀመርኩ፡፡
2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን ጨርሼ ምደባ በማግኘት በግንቦት ወር ላይ ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተጠራሁ፡፡ ስነ-ጽሑፍ ማንበቡንም ሆነ መፃፍ እወደዋለሁ፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላም ደቡብ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ላይ የተለያዩ ግጥሞችን የማቅረብ ዕድል አግኝቻለሁ፡፡ በወቅቱም መማር የፈለኩት ጆርናሊዝም ነበርና ህልሜ ተሳክቶ የትምህርት ክፍሉን ተቀላቀልኩ፡፡ ዘንድሮም የጋዜጠኝነት እና ስነ- ተግባቦት የትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ነኝ፡፡ የትምህርት ክፍሉን ፈልጌ ነው የገባሁት፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡
የአውራ አምባ ማህበረሰብን እንዴት ትገልጪያለሽ? ስንል ላቀረብንላት ጥያቄም፡- የአውራ ማህበረሰብን በራሴ እሳቤ እንዴት ብዬ ልገልጽ እንደምችል አላውቅም፡፡ የአውራ አምባ ማህበረሰብ ለእውነት የቆመ እና ላመነበት ነገር ወደ ኋላ የማይል ማህበረሰብ ነው፡፡ ለታመነበት ነገር እንዴት እስከ ጥግ ድረስ መሄድ እንዳለበት ያየሁበት ነው ብላለች፡፡ በተለይም እዛው ማህበረሰቡ ውስጥ እያለሁ ክፉውም ሆነ ደጉ አይገባኝም ነበር፡፡ ወጣ ሲባል እና እዛው ውስጥ ሲኮን ነገሮች በጣም ይለያሉ፡፡ ምክንያቱም በአውራ አምባ ማህበረሰብ ከልጅነቴ ጀምሮ ነው ያደኩት፡፡ በአውራ አምባ ማህበረሰብ የሴት እና የወንድ፣ የእናት አና የአባቴ፣ ከእህት እና ከወንድሞቼ ጋር ያለውና እንዲሁም በሰፈር አካባቢ ያለው መልካም ግንኙነት ነው፡፡ ምንም ዓይነት ፖሊስ እና ፍርድ ቤት እንዲሁም እስር ቤት በአወራ አምባ ማህበረሰብ የለም፡፡
በማንኛውም ወቅት ሰላማዊ ኑሮ የኖረ ማህበረሰብ ነው፡፡ የአውራ አምባ ማህበረሰብ በ1964 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት 50ኛ ዓመቱን አክብሯል፡፡ ዘንድሮም ወደ 52 ተኛ ዓመት ተሻግሯል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ምንም ዓይነት ግጭት የሌለበት እና ሰላማዊ ሆኖ ያለፈ ማህበረሰብ ነው። ከእዛ ወጥቼ ሰላማዊ ያልሆነውን አካባቢ ስመለከት ይህም አለ ለካ? አስብሎኛል፡፡ እዛው ሲኮን ነገሮች ተገልጠው አይታዩም። ምክንያቱም ምንም ዓይነት ዓዲስ ነገር ያለ አይመስልም፡፡ ልዩነቱም አይገባኝም፡፡
የአውራ አምባ ማህበረሰብ ለእኔ ያሳየው የራስን መንገድ ተከትሎ ላመነበት ነገር እስከ ጥግ ድረስ መሄድን ነው፡፡ ልክ ናቸው ብሎ የተቀበላቸውን ነገሮች እየተገበረ ለሰው እየገለጠ የሚሄድ ነው ፥ ህዝቡ፡፡ በራሴ እሳቤ ድርጊት እና ቃል በአንድ የሄዱለት ማህበረሰብ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚያ ማህበረሰብ የተነገሩ ነገሮች ሁሉ ዝም ብለው የቀሩ አይደሉም፡፡ የእውነት እየኖሩበት ነው፡፡ እኩልነት ዝም ብሎ አይደለም የሚነገረው እየተነገረ ነው የሚኖረው፡፡ ሰላም ለሰው ልጆች ያስፈልጋል ሲባል ዝም ብሎ ሳይሆን እየተኖረ ሰላምን ማሳየት ነው፡፡ እኔ እዛው ማህበረሰብ ካለው ቤተሰብ በልቼ እርስ በእርስም ተዋውቀን ተጠያይቀን ነው ያደግነው በክረምት ከትምህርት ቤት ስመለስ ሁሉንም ቤተሰብ ዞሬ ነው ሰላም የምለው፡፡
በተመሳሳይም ሁሉም ሰው ስሞኝ እና ትምህርት እንዴት ነው ብሎ ነው የሚጠይቀኝ። በአውራ አምባ ማህበረሰብ ውስጥ ሁሉም ሰው አብሮ ነው የሚተሳሰበው፡፡ ይህም ወጥቼ ሳየው ነው የገባኝ፡፡ የሚናገረውን የሚኖር እና የኖረውን የሚናገር ማህበረሰብ ነው ያለው፡፡ ለእኔ የአውራ አምባ ማህበረሰብ ልክ እንደማወራው ነው፡፡ እኔ አንደ እድል ነው በአውራ አምባ ማህበረሰብ የተገኘሁት፡፡ ወላጆቼ ናቸው መርጠው ያገኙት እኔ ግን ተወልጄ ነው፡፡ በዚህም ማህበረሰብ ተወልጄ በማደጌ ተስፋ አልቆርጥም፡፡ ምክንያቱም ከእነሱ የተማርኩት ይህንን ነው፡፡ ወላጆቻችን መስራቹን ጨምሮ የቀለም ትምህርት ያገኙ አይደሉም፡፡ ግን መደበኛ የቀለም ትምህርት አገኘን ተብሎ ከሚታሰበው ሰዎች እውቀት በላይ ይዘው ያገኘኋቸው ሰዎች ናቸው፡፡
ሁሉንም ነገር ከመጀመሪያው ስትፈትሽ የህፃናት መብት አጠባበቅ በማህበረሰቡ በግልጽ አለ፡፡ በሌላ ጎን ሴት ከወንድ እኩል ናት፡፡ ለእህቶቻችን ለእናቶቻችን እኩል የሚታዩ ሲሆን ስራ በእኩልነት እንጂ በአውራ አምባ ማህበረሰብ በፆታ መከፋፈል የለም፡፡ ማድቤት ገብቶም ይህ የሴት ስራ ነው ብሎ ወደ ጎን መተው ሳይሆን ማድቤት ገብተው ይጋግራሉ እርሷም የወንድ ስራ ነው ማለት የለም በሬ ጠምዳ ታርሳለች፤ ትሸምናለች፡፡ ሁሉም ሰው ከአንድ ከሰው ዘር ምንጭ ነው የተገኘነው፡፡ ባዕድ መባባሉን ከየት ነው ያመጣነው፡፡ ሁላችንም እህትና ወንድም ነን ብሎ ማሳየትን ቀለም መቁጠር ብዙ ነገር አለው ያሰቡትን ነገር ለማድረግ ቀለም አለመቁጠራቸው ከምንም ነገር አላገዳቸውም፡፡
የአውራ አምባ ማህበረሰብ የራሳቸውን ነገር ይዘው ሲመጡ የአካባቢው ማህበረሰብ አልተቀበሏቸውም ነበር፡፡ እስከ ስደት ድረስ ደርሰው ነበር፡፡ አሁን ያለውን ማንነት እስኪያገኙ ድረስ ብዙ መንገላታት ደርሶባቸዋል፡፡ ያንን ነገር ዞር ብዬ ሳየው ቀለም ባልቆጠረ አንደበት ያሁሉ ችግር እና ፈተና ሲመጣ ተቋቁሞ መያዝ እንደ ስኬት ነው የማየው፡፡ ከዛ ማህበረሰብ ወጥቼ ለመላመድ እጅግ የተቸገርኩ ቢሆንም እንኳን በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ እንኳን ወጣሁ ያስባሉኝ ነገሮች ብዙዎች ነበሩ፡፡
ምክንያቱም ብዙ ነገር ተምሬበታለሁ፡፡ የአውራ አምባ ማህበረሰብ በብዙ መንገድ የተለየ ነው፡፡ አይናዲስ የነገረችንም ይህንኑ ነው፡፡ አውራ አምባ ማህበረሰብን ከሌሎች ልዩ የሚያደርገው በአውራ አምባ ማህበረሰብ የሰርግ ስነ- ስርዓት የለም፡፡ ትዳር አለ ነገር ግን ድግስ የለም፡፡ ወንድ ከ19 ዓመት በላይ ሴቷ ከ18 ዓመቷ በላይ ሲሆን እሷም ሆነ እርሱ የመረጡትን ሰው በፍላጎታቸው ያገባሉ፡፡ ጋብቻውም በአካባቢው ባሉት ሽማግሌ እማኞች ነው የሚታሰረው፡፡ በኋላም የጋራ ንብረታቸውን ያስመዘግባሉ፡፡
በማህበረሰቡ ትዳር ሲመሰረት ለትዳሩ እንጂ ትልቅ ቦታ ያላቸው ለድግሱ አይደለም፡፡ ለሰርግ ተብሎ ያለአግባብ ከሚወጣው ወጪ ይልቅ ትኩረቱ ለወደፊት ህይወታቸው ይሰጣል። እኔ የማምነው የሰው ልጅ አንድን ህይወት ልክ ነው ብሎ ከተከተለ የማይደርስበት የለምና ወደ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከመጣው በኋላ ብዙም አልተቸገርኩም፡፡ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ላይ ከዚያ ማህበረሰብ የመጣን ተማሪዎች የተለያየ የትምህርት ክፍል ብንገባም እንደ ባዳ ሳይሆን እንደ ቤተሰብ ነው የምንተያየው፡፡ ምክንያቱም በአውራ አምባ ማህበረሰብ ለልጆች ሁሉም አባት እና እናት እንዲሁም ቤተሰብ ነውና፡፡ በዚህም እሳቤ ነው ያደግነው፡፡ ወደ አዲስ አካባቢ በመምጣቴ ለአዲስ ነገር እራስን ዝግጁ ማድረግን ተምሬበታለሁ፡፡
በቆይታዬም የተለያየ ባህሪ ያላቸውን ሰዎችንም ማየት በመቻሌ ዕድለኛ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ እንዴት ሆኜ ከሰዎች ጋር መኖር እችላለሁ የሚለውን አይቼበታለሁ። ወደፊትም በስራ አጋጣሚ የትኛውም ሴክተር ብገባ ከሰዎች ጋር እንዴት መኖር እና መግባባት እንደምችል ተሰርቻለሁ ማለት እችላለሁ። ይህንንም መማር በመቻሌ ትልቅ ነገርን አትርፌበታለው፤ ተምሬበታለውም ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከእኔ ተምረዋል ብዬ የማስበው ደግሞ የትም ቦታ ብሄድ እኔነቴን ደብቄው አላውቅም፡፡
ከአውራ አምባ ማህበረሰብ መምጣቴንም በግልጽ ነው የምናገረው፡፡ አውራ አምባ ማህበረሰብን በስም ብቻ የሚያውቁ እና በጥልቀት ለማያውቁ ሰዎች እንዲያውቁ ትልቅ በር ከፍቼላቸዋለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡ አውራ አምባ ማህበረሰብ የት ነው የሚኖረው፣ ምንድነው የሚሰራው፣ በምን ነው የሚያምነው የሚለውን እንዲያውቁ መንገድ ከፍቻለሁ ማለት እችላለሁ፡፡
በተለይም አሁን ባለንበት ዓለም ውስጥ ስኖር ተወዳዳሪ ሆኜ መውጣት አለብኝ የሚል የራሴ እሳቤ አለኝ፡፡ የራሴንም አቅም በብዙ መንገድ ማሳደግ አለብኝ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ከገባው ጊዜ ጀምሮ መጀመሪያ ላይ ክበባቶችን ማየትና መጎብኘትን እና ንቁ ተሳትፎ ማድረግን እፈልግ ነበር፡፡ እነዚያ ነገሮች በደንብ ተሳክተውልኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብዙ ሰዎች መምህራኖች፣ተማሪዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች ሁሉ ያውቁኛል ህልሜንም አሳክቻለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ የታወኩበትም ከአውራ አምባ ማህበረሰብ ስለመጣው ብቻ ሳይሆን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ “የምክንያታዊ ባለራዕዮዎች ስብስብ” የሚል ክበብ አለ፡፡ ክበቡ ከ13 ዓመታት በላይ የተሻገረ ነው፡፡ እዛ ክበብ ውስጥ በመጀመሪያ ዓመት የመጀመሪያ ሴሚስተር ጀምሮ እከታተል እና እሳተፍ ነበር፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ ትልልቅ ሰዎች እየመጡ ይጋበዙ ነበር፡፡
አንጋፋ እና ሞዴል ደራሲያንን እንግዳ በማድረግ በአካል ተገኝተው የህይወት ልምዳቸውን ያካፍሉ ነበር፡፡ ከዚህም ክበብ ብዙ ልምድ ተካፍየበታለው። ለቀጣይ ህይወት የሚሆኑኝን ብዙ ልምዶችን ወስጄበታለው፡፡ በዚህም ጥሩ እንቅስቃሴ ስለነበረኝ ወደ አመራርነት መምጣት ቻልኩ፡ ፡ አሁን ላይ በክበቡ በፕሬዜዳንትነት ነው እያገለገልኩ ያለሁት፡፡ ወደ ክበቡም መግባት የፈለኩት በሰዎች ፊት መናገር መቻል እና በማንኛውም ቦታዎች ተወዳዳሪ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆንን እፈልጋለሁ እንጂ “አንድ ቦታ ላይ ብቻ ታጥሬ መቅረትን አልፈልግም”፡፡ በተለይም በብዙ ጫናዎች ውስጥ ሆኜ መስራት እችላለሁ ወይ የሚለውን ማየት እፈልግ ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ በክበባት ላይ በጣም መስራት እና ጥሩ ውጤት ማምጣት እፈልግ ነበር፡ ፡ ሁለቱንም ግን እንዴት አጣጥሜ አስኬዳለሁ እል ነበር፡፡ በዘንድሮው ዓመት በክበብ ውስጥ ጥሩ እንቅስቃሴ ነበረኝ፤ በዚህም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከአራት በላይ ኢቨንቶችን ማዘጋጀት ችለናል፡፡
በትምህርቴም በዘንድሮ ዓመት ሶስት ሴሚስተር ነበር የምወስደው፡፡ የጆርናሊዝም ትምህርት ከባድ፣ አሳይመንቶች እና ተግባር የሚበዛበት የትምህርት ክፍል ነው፡፡ በዚህም በጣም ተጨናንቄ እና ከቁጥጥሬ የወጣ መስሎኝ ነበር፡፡ በክበቡም ጥሩ የሚታይ ነገር የሰራሁበት እና በትምህርቴም በሶስቱም ሴሚስተር 3.86 በመስራት ከፍተኛ ውጤት ያመጣሁበት፣ እራሴን ያየሁበት እና እንደምችልም ያመንኩበት ጊዜ ነበር፡፡ ስለዚህም እንደምፈልገው በተጽዕኖ ውስጥ ሆኜ የምፈልገውን ነገር ማድረግ እንደምችል ያየሁበት እና በቀጣይ ዓመትም የፈጣሪ ፈቃድ ከሆነ ብዙ ስራዎችን የምስራበት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ በዚህ ብቻ ሳልገታ በሀዋሳ ኒቨርሲቲ ውስጥ ወደ 17 የሚሆኑ ክበባት አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ወደ ስድስት በሚሆኑት ውስጥ አባልም ጥሩ ተሳታፊም ነኝ፡፡ ሌላኛው ክበብ ጆኦኢሲሳ(ጆርናሊዝም ኤንድ ኮሚዩኒኬሽን ስቱደንት አሶስየሽን) የሚባል ክበብ የእኛ የትምህርት ክፍል አለ፡፡ በዚህም ክበብ መሪ ሆኜ ነው የምሰራው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሀዋሳ ኢንዳስትሪያል ፓርክ የማህበረሰብ ሬድዮ 102.4 ውስጥ ሁለት ሳምንታዊ ፕሮግራም አለን። አርብ በ8፡00 ሰዓት የሚደመጥ “ቅርጽ ያልያዙ እይታዎች” የሚል እና ቅዳሜ በ9፡00 “ቅኝት ጓዳ” የሚል ፕሮግራም አለ፡፡ በቀጣይ ዓመትም የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ስለሆንኩ በተሻለ መልኩ ለመስራት አስባለሁ፡፡ በሁሉም ዘርፍ ንቁ ተሳታፊም ነኝ፡፡ በመጨረሻም በሁለት ነገር ላይ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ አንደኛ እኔን የሚያገናኘኝ አውራ አምባ ማህበረሰብ ነውና ስለአውራ አምባ ማህበረሰብ ሲወራ ወይም አንድ ነገርን ብቻ ልናውቅ ስለምንችል የአውራ አምባ ማህበረሰብ ምንድነው የሚሰራው? እንደ ሀገር ምንድነው የምንጠቀመው? የሚለውን ብናውቅ፣ ብናለማው እና በየአካባቢያችን ሁላችንም ብንጠቀመው እንደ ሀገር እናተርፍበታለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ቦታው ድረስ መሄድ ካልቻልን ግን ከመስራቾቹ አንደበት ወይም ዩቲብ ቻናል በመከታተል የአውራ አምባ ማህበረሰብ ይዞት የመጣው ምንድነው? የሚለውን እስከ ዛሬ ድረስ 50 ዓመታትን ይዞት የመጣውን እና የሴቶችን እኩልነት ያሳየው፣ የህፃናትን መብት እና አቅመ ደካሞችን መከንከባከብ ቀላል ነገር አይደልም ለእኔ፡፡ በተለይም ሌሎች ስላደረጉ ሳይሆን የእኛ ቦታ የቱ ጋር ነው? ሌሎች ስላደረጉ ለእኔ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ማንነታችንና ባህሪያችን የተለያየ በመሆኑ ለእኛ የሚሆነን ነገር ስላይደለ በእውነት የተገኘውን ነገር ብንፈትሽ እና ብናውቅ ውጤታማ ልንሆን እንደምንችል መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
More Stories
“ሳንቲም ሲጥሉልኝ አመስግኜ ነው የምመልሰው” – ወጣት ማህቶት በለጠ
“ጥበብ ነገሮችን በተለየ መንገድ ማየት መቻል ነው” – ተወዛዋዥ ተስፋ ጽዮን ንጉሴ
ትኩረት ሊሰጠው ይገባል!