የታላቁ ህዳሴ ግድብን እንዳጠናቀቅን ሁሉ የባህር በርን ለማስመለስ የሚደረገውን ጥረት በይበልጥ ማገዝ እና መደገፍ እንደሚገባ ተጠቆመ

የታላቁ ህዳሴ ግድብን እንዳጠናቀቅን ሁሉ የባህር በርን ለማስመለስ የሚደረገውን ጥረት በይበልጥ ማገዝ እና መደገፍ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 22/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሁላችንም አሻራ ያረፈበት የታላቁ ህዳሴ ግድብን እንዳጠናቀቅን ሁሉ የባህር በርን ለማስመለስ የሚደረገውን ጥረት በይበልጥ ማገዝ እና መደገፍ እንደሚገባ የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

‎”ከጂኦ ስትራቴጂ ኩስምና ወደ ታደሰ ቁመና” በሚል መሪ ሀሳብ ለአርባ ምንጭ ከተማ የፖሊስ አመራሮች እና አባላት ስልጠና እየተሰጠ ነው።

‎የአርባምንጭ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ክበበው አዳል፥ የፖሊስ ሰራዊት ቁመናው እንዲስተካከል በተሰራው ያላሰለሰ ጥረት ሰፊ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቁመው፥ እንደ ሀገር በተመዘገቡና እየተመዘገቡ በሚገኙ እምርታዎች የፖሊስ አመራሩና አባሉ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ሀገራችን “ከኩስምና ተላቃ ወደ ላቀ ቁመና” መድረስ እንድትችል ቁርጠኛ ልንሆን ይገባል ብለዋል።

‎የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሀይሶጼ ሂሎታ በስልጠናው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ከለውጡ ወዲህ የሁሉንም አቅም ለመገንባት በሁሉም መስክ እንደ ሀገር የተለያዩ ስልጠናዎች እየተሰጡ መቆየታቸውንና በዚህም ለውጦች መመዝገባቸውን አብራርተዋል ።

‎ሀገራችን በእድገት ከፍታ እንዳትሄድ የውስጥና የውጭ ባዳዎች እያደረሱ ያለው ተጸእኖ ከፍተኛ እንደሆነ የገለፁት አቶ ሀይሶጼ፥ ይሄንን የባንዳዎችን እቅድ በማክሰምና የውስጥ ጸጋዎቿን አሟጦ በመጠቀም በጋራ የማደግ ስትራቴጂን ልናሳካ ይገባል ብለዋል።

‎ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ማንሰራራት ዘመን የመጣችበትን ቁመና በመረዳት የፖሊስ፣ አመራሩና አባሉ በዚህ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው ያሉትየመንግስት ዋና ተጠሪው፥ የሁላችንም አሻራ ያረፈበት የታላቁ ህዳሴ ግድብን እንዳጠናቀቅን ሁሉ የባህር በር ለማስመለስ የሚሰራውን ተግባር ማገዝ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

‎በስልጠናው በከተማው ከሁሉም ቀበሌያት የተውጣጡ የፖሊስ አመራሮችና አባላት ተሳታፊ ሲሆኑ ስልጠናው ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

‎ዘጋቢ፡ ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን