የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ልዩ ተኩረት ሊሰጥ ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 02/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ልዩ ተኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ።
በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ2 መቶ 50 ሺህ በላይ ለሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩም ተገልጿል።
የክልሉ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ያዘጋጀውን የምክክር መድረክ በንግግር የከፈቱት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ አስተዳድርና የቢሮው ኃላፊ አቶ ገ/መስቀል ጫላ እንደተናገሩት በክልሉ የክህሎት መር ስራ ዕድል ፈጠራ ስራ የወጣቱን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ይገኛል።
ሀገር የዜጎች ድምር ውጤት መሆኑን የገለፁት የቢሮው ኃላፊው የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በክልሉ ስራ አጥነትን ለመቀነስ በተደረጉ ጥረቶች አበረታች ውጤት መመዝገቡንም አቶ ገ/መስቀል ተናግረዋል።
በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ2 መቶ 50 ሺህ በላይ ለሚደርሱ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ስለመፈጠሩም ተናግረዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው የጠንካራ መንግስት መለያው የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
ሀገሪቱ ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ልዩ ተኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህ ረገድ ዘርፉን በጠንካራ አቋም መምራት ይገባልም ብለዋል።
የማምረቻና የብድር ማመቻቸት ስራው ለስራ ዕድል ፈጠራ ጤናማነት አስተዋፅኦው የላቀ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በይበልጥ በግብርናው ዘርፍ በርካታ ወጣቶችን ማሰማራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ባለሙያዎች በኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ
የባስኬቶ ዞን ተወላጆች የአንድነት መድረክ ማጠቃለያ እየተካሄደ ነው
በእንስሳት እርባታ ከተሰማራን ወዲህ ኑሯችን ተሻሽሏል – የጋዘር ከተማ ወጣቶች