የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያውን ተከትሎ ምርቶችን በሚደብቁና የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የኣሪ ዞን ንግድና ገቢያ ልማት መምሪያ አሰታወቀ

የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያውን ተከትሎ ምርቶችን በሚደብቁና የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የኣሪ ዞን ንግድና ገቢያ ልማት መምሪያ አሰታወቀ

የንግዱ ማህበረሰብም የኑሮ ዉድነቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲታቀብ ጥሪ ቀርቧል።

በኣሪ ዞን የጂንካ ከተማ ነዋሪዎችም በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት እንደሀገር እየተከናወነ ያለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ ባልተገባ መንገድ ዋጋ ጭማሪ በማድረግ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት የሚደረገው ስግብግብነት ተቀባይነት የሌለው ህገ ወጥ ተግባር መሆኑን ገለጸው መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

እንደሀገር የተጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዉን ምክንያት በማድረግ ምርቶችን በሚደብቁና የዋጋ ጭማሬ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የተናገሩት የኣሪ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደርበው ጠቃቦ፤ በሸቀጦች፣ በግንባታ ዕቃዎችና በምግብ ነክ ፍጆታዎች ላይ ዋጋ ጭማሪ መደረጉን ተከትሎ የሚደረገውን ቁጥጥር ማህበረሰቡ ጥቆማ በመሰጠት እንዲደግፍ አሳስበዋል።

የመምሪያ ኃላፊው አክለውም ከዚህ ቀደም በእጃቸው በነበሩ መሰረታዊ ፍጆታ ዕቃዎችና በግብርና ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪና ምርት በሚደብቁ ንግድ ድርጅቶች ላይ ደንቡንና መመሪያውን ተከትሎ በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

የጂንካ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተካ አየለ ምርት በመደበቅና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውን በኢንስፔክሽን ቁጥጥርና ክትትል ስራዎች ማረጋገጥ የተቻለ በ50 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማሸግና በህግ ቁጥጥር ሥር ዉላው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት ምርት በመደበቅ ከቦታ ቦታ የሚያንቀሳቅሱ ነጋዴዎችን ጥቆማ በመስጠት ከኢንስፔክሽን ቡድኑ ጎን እንዲሆን የጂንካ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተካ አየለ አሳስበዋል።

የዋጋ ንረት እንዲጨምርና የህዝቡ የኑሮ ሁኔታ እንዳይረጋጋ በማድረግ የምርት አቅርቦት ዕጥረት እንዲፈጠር የግብርና ምርቶችንና መሰረታዊ የምግብ ፍጆታ ዕቃዎችን በመደበቅ የንግድ አሻጥር በመፍጠር ህዝቡን እየበዘበዙ ባሉ ህገ ወጦች ላይ ፖሊስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ ነው ያሉት የኣሪ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሽብሩ አማራ ናቸው።

በዞኑ በሁሉም ወረዳዎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የፀጥታው መዋቅር ከንግድና ገበያ ልማት መዋቅር ጋር በመሆን ህገወጥ የዋጋ ጭማሪንና የአቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም በቅንጅት በተሠራው ሥራ በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችና የታሸጉ የንግድ ተቋማት መኖራቸውን ኢንስፔክተር ሽብሩ አማራ ተናግረዋል።

መንግስት የኢትዮጵያን የምጣኔ ኃብት እድገት በተሟላ መልኩ ለማስቀጠልም አሁን ላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሙሉ ትግበራ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪና የአቅርቦት ችግር እንዲፈጠር በሚያደርጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ እርምጃ በመውሰድ የተረጋጋ የኑሮ ሁኔታ እንዲፈጠር እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል።

ዘጋቢ፡ ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን